Search

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታና የኢንቨስትመንት መስህብ እየቀየሩ የሚገኙ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች

ሰኞ ኅዳር 07, 2019 183

ኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ፣ የደመቀ ባህል እና የበለጸገ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ እነዚህን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ገቢ በመቀየር ረገድ የመሠረተ ልማት ውስንነትና የመዳረሻዎች አለመልማት ዓብይ ማነቆ ሆነው ቆይተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥ ያለሙት የኮሪደር ልማት፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የተሰኙ ሦስት የተሳሰሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች በኢትዮጵያ የልማት ምኅዳር ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች እየተስፋፋ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እያሳለጠ ይገኛል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ፣ ንጹሕ፣ ብርሃን ያላቸው፣ ለእግረኛ እና ለብስክሌት ምቹ ጎዳናዎች እንዲሁም አዳዲስ መናፈሻዎች መገንባታቸው ዓለም አቀፍ እንግዶች በከተማዋ የሚኖራቸውን ቆይታ እንዲያራዝሙና የስብሰባ ቱሪዝም (MICE) እንዲነቃቃ አስችሏል።

የመንገዶች መስፋትና የትራፊክ ፍሰት መሻሻል የሎጂስቲክስ ወጪን እና ጊዜን የቀነሰ ሲሆን፣ በኮሪደሮቹ ዳርና ዳር የተገነቡ ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የገበያ ዕድል ፈጥረዋል።

ዘመናዊ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በመሬት ውስጥ በመቅበር የተከናወነው ግንባታም፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ለዘመናዊ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማረጋገጫ ሆኗል።

በገበታ ለሸገር የተጀመረውን የኢኮ-ቱሪዝም ልማትን በማስፋት የተተገበረው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያን ከተለመደው የታሪክ እና የቅርስ ቱሪዝም ባለፈ ወደ ሥነ-ምኅዳር እና የመዝናኛ ቱሪዝም አሸጋግሯታል።

በዚህ መርሐ ግብር የለሙት ወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ ቀደም ሲል በመንገድ፣ በመብራት እና በማረፊያ እጥረት ምክንያት ለጎብኚዎች ዝግ የነበሩ ውብ ሥፍራዎችን ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከላት ቀይረዋቸዋል።

ይህም በግንባታው ወቅት በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፣ አካባቢውን ማኅበረሰብ የዘላቂ የቱሪዝም አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል።

ከነዚህ ስኬቶች በመነሳት የተጀመረው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ደግሞ፣ የተፈጥሮና ባህላዊ ሀብቶችን ከመጠበቅ ባለፈ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማካተት እንደ ሎጎ ሐይቅ፣ ባሌ ተራሮች እና ሌሎች ክልላዊ መዳረሻዎችን በማልማት ላይ ይገኛል።

የዚህ ፕሮጀክት ልዩ ባሕሪ የአካባቢ ጥበቃን ከዘመናዊ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ጋር አጣምሮ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ሀብት መፍጠሩ ነው።

እነዚህ ሦስት ፕሮጀክቶች የመንግሥትን በጀት ብቻ ሳይጠብቁ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን፣ የንግድ ተቋማትን እና ባለሀብቶችን በገንዘብ እና በዕውቀት በማሳተፍ አዲስ የሀብት ማሰባሰብ ባህል ገንብተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከድርቅ እና ከግጭት ጋር ተያይዛ የምትነሳበትን ትርክት በመቀየር፣ ዘመናዊ ከተሞችን እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎችን የምትገነባ መሆኗን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

በአጠቃላይ እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮና የታሪክ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ሀብት ለመቀየር የጀመረችው ስትራቴጂያዊ ጉዞ ሕያው ማሳያዎች ናቸው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: