በትግራይ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መከፈል መጀመሩን ጨምሮ፣ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸው በነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል።
በመቐሌ ከተማ በተካሄደ ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙ ነዋሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባለአደራ አስተዳደሩ እና መንግሥት የጀመሩት የሰላም ጉዞ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መከፈል መጀመሩ ከፍተኛ ኩራትና እፎይታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፣ ይህ መልካም ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የተጓደሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለሁሉም እንዲደርሱ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ ቤት፣ ውኃ፣ ምግብ እና ሰላም ነው የምንፈልገው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ነዋሪዎች፣ ያለፈው አልፏል፣ የጠፋው ጠፍቷል፤ አሁን ግን እኛ ያለነው ለሰላም ዘብ በመቆም ሰላምን በመዘመር ላይ ነው በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።
የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋት የኮሪደር ልማት ሥራዎች በአስቸኳይ እንዲጀመሩና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።
ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ (DDR) ሂደት በቀጣይነት እንዲተገበር የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ይህ ሂደት በተግባር ሲረጋገጥ በበረሃ የሚገኙ ወገኖች ሳይዘገዩ ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል።
የተጀመረው ሰላማዊ ጉዞ ለሁሉም አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛላቂ ሰላም እንዲሰፍንም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: