Search

የዛሬዋ ታዳሚ የነገዋ አዘጋጅ ሀገር ኢትዮጵያ ከኮፕ 31 ጉባኤ እየቀሰመች ያለው ልምድ

እሑድ ኅዳር 06, 2019 245

በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ የሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP31፣ ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት በአዲስ አበባ ለምታስተናግደው COP32 ጉባኤ ወሳኝ የልምድ ማግኛ እና ስትራቴጂያዊ የዝግጅት ምዕራፍ ሆኗል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬቶች፣ የንጹህ ኢነርጂ መሠረተ ልማት ግንባታ ተሞክሮዎች እንዲሁም የቀጣይ በካይ ጋዝ ልቀት ስጋቶችና መፍትሄዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጋርተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና በገንዘብ ሚኒስትርና የኮፕ 31 ዋና ተደራዳሪ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማካሄድ አጋርነቱን እያጠናከረ ይገኛል።

ከዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ጎን ለጎን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ የኮፕ32 ዝግጅቶችን ከወራት በፊት ጀምሮ ወደ ተግባር አስገብቷል። ኮሚቴው በመጪው ዓመት አዲስ አበባን የሚጎበኙ ከ80 ሺህ በላይ እንግዶችን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችሉ የሆቴል፣ የትራንስፖርት እና የመሠረተ ልማት አቅሞችን በዝርዝር እየገመገመና እያሻሻለ ይገኛል።

በአሁኑ የኮፕ31 ጉባኤ አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችና ክፍተቶች ለኢትዮጵያ የዝግጅት ምዕራፍ እንደ ጠቃሚ ግብዓት እየተወሰዱ ናቸው። የኮፕ 32 ጉባኤን በስኬት ማስተናገድ ከመንግሥት ጥረት ባለፈ የሁሉንም ዜጎች ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሏን ለዓለም የምታሳይበት ወርቃማ አጋጣሚ ይሆናል።

 

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: