አርሰናል የአሁኑ ተፎካካሪነቱን ለመገንባት እና ከቀውስ ለመውጣት በትክክለኛው ፍኖት ባለ ጊዜ ወይንም የማርቲን ኦዴጋርድን ዝውውር ከማጠናቀቁ፣ አሮን ራምስዴልን ከማስፈረሙ፣ ቤን ኋይትና ታኬሄሮ ቶሚያሱን ወደ ኢምሬትስ ከማምጣቱ አስቀድሞ ብዙም ትኩረት ያላገኘን ፊርማ በ2021 የሐምሌ ወር መባቻ ሰሞን አግኝቶ ነበር።
መድፉ አስቀድሞ በቆመ ኳስ የሚጠቃ፣ የቆመ ኳስ ለመከላከል የሚቸገር ነበርና ሁልጊዜም ከጋዜጠኞች ለሚነሱለት ጥያቄዎች መሻሻል አለብን ሲል የቆየው ማይክል አርቴታ ለጋዜጠኞች ይህን አለ። “በዚህ ዘርፍ ሊቅነት ገበያው ላይ የማውቀው አንድ ሰው አለ። እርሱ እኛን ተቀላቅሏል። ለእኛ እጅጉን ጠቃሚ ነው። ስሙ ኒኮላስ ጆቬር ይባላል። ከዚህ በፊት በማንቺስተር ሲቲ አብሬው ሰርቻለሁ” በማለት በአንድሬስ ጂኦርገሰን ምትክ ኒኮ መምጣቱን አበሰረ።
ከዚያ በመለስ ያለው የአርሰናል የቆመ ኳስ ታሪክ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነው።በወቅቱ ዝውውሩን እንደ ነገሩ የተመለከቱት ብዙዎች ነበሩ። በአንፃሩ የኒኮን ሂደት ለሚያውቁ፣ በሞንፔሌ ፣ በብሬንትፎርድ እና ሲቲ ቤት የነበረውን ሚና ለተረዱ ግን አርሰናል ክፍተቱን ሊቀርፍ የሚችል ባለሙያ አገኘ ነበር ያሉት።
የሸብራክ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ምሩቁ ኒኮላስ ጆቬር ለትምህርት ካናዳ በነበረበት ጊዜ በአሜሪካ እግር ኳስ ተማርኮ ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት መስጠት ጀመረ። ኳስ መጫወት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ጉዳት ሰንኮፍ ሆኖበት መጫወቱን አቁሞ ማሰልጠንን አሰበ።
ወደ አውሮፓ ሲመለስም በአሜሪካ እግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች ለጥቃቅን ጉዳዮች የሚሰጠውን ትኩረት መዝግቦ እና በልቡ ስሎ ነው። በሞንፔሌ የምስል ተንታኝ የነበረው እሱ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠጠር ከ2012 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ግን የቆመ ኳስን በልዩነት ያጠና ነበር።
ህልሙ እውን ሆኖለት በ2016 በብሬንትፎርድ የቆመ ኳስ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ። ቀደም ብሎ ዲን ስሚዝ በኋላም ቶማስ ፍራንክ በስራው ተገረሙበት።
በብሬንፎርድ የሦስት ዓመታት ቆይታው 46 የቆሙ ኳሶች እንዲቆጠሩ ምክንያት ሆነ። ይህ ስራው ማንቸስተር ሲቲን ሳበ። ግን በስራው የበዛ ትኩረትን ያገኘው በማይክል አርቴታ ዘንድ ነበር።
አርቴታ ፔፕን አሳምኖ የጆቬር መዳረሻ ኢቲሃድ ሆነ። ጆቬር ሥራው አስደናቂ ሆኖ ሳለ የሚሰጠው ክብር ግን እምብዛም አይደለም። በዚህ ይበሳጭ ነበር ይላል የጊቭምስፖርት ዘገባ። ይባስ ብሎም አርቴታ የአርሰናል አሰልጣኝ ሆኖ ክለቡን ለቀቀ።
ፕሪሚየር ሊግ ድረ-ገፅ ላይ የወጣ ቁጥራዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በሲቲ ቤት የመጀመሪያ ቆይታው ስራው ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ ከቆመ ኳስ የሚቆጠርባቸውን ጎሎች መቀነስ ነበር። በዚህም እሱ ቡድኑን ከመቀላቀሉ በፊት ይቆጠርበት ከነበረው 39 በመቶ ወደ 20 በመቶ ቀንሶታል። በሁለተኛ ዓመት ቆይታው ደግሞ ወደ 16 በመቶ አውርዶታል።
ትኩረት አልተሰጠኝም ብሎ እንዲሁም በአርቴታ ፕሮጀክት ተማርኮ ማንቺስተር ሲቲን ለቆ መድፈኞቹን ተቀላቀለ። የአርሰናል የቆመ ኳስ ታሪክም ተቀየረ።
አርሰናል በየዓመቱ ከ20 በላይ ጎሎችን የሚያስቆጥር አጥቂ ባይኖረውም በዓመት ከ15 እስከ 20 ጎሎችን የሚያስገኝ ሐሳባዊ የቆመ ኳስ አሰልጣኝ ግን አለው። እያደር እያደር አዳዲስ ነገሮችን እየጨመረ የማስቆጠሪያ ስልትን የሚፈጥር ሆኗል። የቆመ ኳስ አጠቃቀምን ያዘመነ እና አስፈሪነቱን የጨመረ አሰልጣኝ-ኒኮላስ ጆቬር።
ባለፈው ረቡዕ አርሰናል ማንቺስተር ዩናይትድን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ መድፈኞቹ 13 የማዕዘን ምቶችን ሲያገኙ 13ቱም ለ'ቀያይ ሰይጣኖቹ' ችግር የፈጠሩ፣ ምን እያደረጉ እንደሆነ ለመረዳት የቸገራቸው፣ ሳጥኑ ውስጥ የነበረው የአርሰናል ተጫዋቾች የዘገየ ሩጫ የዩናይትድ ተጫዋቾች ራስ-ምታት ነበር።
ይህ ሰው እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠጠር በ2021 አርሰናልን ከተቀላቀለ በኋላ መድፈኞቹ ከማዕዘን ከሚሻገሩ ኳሶች 48 ግቦችን አስቆጥረዋል። ይህም በአማካይ ከ16.4 የማዕዘን ምቶች አንዱን ወደ ጎል ይቀይራሉ ማለት ነው። ግቦቹ መቆጠራቸው ብቻ ሳይሆን አርሰናል እያንዳንዱን የማዕዘን ምት ሲያገኝ ተጋጣሚ መራዱ ነው። አሁን ሁሉም ቡድኖች የአርሰናል የማዕዘን ምትን እንደ ፍፁም ቅጣት ምት የሚፈሩት፣ የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኞች ያችን ሰዓት የሚጨነቁላት ሆናለች።
ፈረንሳዊው የማይክል አርቴታ ረዳት አሰልጣኝ እና ቀኝ እጅ ኒኮላስ ጆቬር ወደ አርሰናል ከመምጣቱ በፊት መድፈኞቹ ባደረጓቸው 111 ጨዋታዎች ላይ በተሰራ ቁጥራዊ መረጃ አርሰናል ከማዕዘን ምት የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ትንሽ ነበሩ። በየ 32 የማዕዘን ምቶች አንድ ጎል ነበራቸው። አሁን ግን በ16.4 የማዕዘን ምት ጎል አለው።
ለአርሰናል የቆመ ኳስ ምስጢራዊ የማጥቃት መሳሪያው ነው። የቡድኑ የማጥቃት መሪ፣ የመከላከል አስጀማሪ፣ እና የቡድኑ ኮንዳክተር ማርቲን ኦዴጋርድ በተጎዳ ጊዜ የቆመ ኳስ የማሸነፊያ መንገዱ ነበር።
አሁን አሰልጣኞች የሚያወሩት ስለ አርሰናል የቆመ ኳስ አደገኛነት ነው። ቁመተ-መለሎዎቹ የአርሰናል ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ አጫጭሮቹም በግንባር እየገጩ ያስቆጥራሉ። ወደ ሳጥን የሚላኩት የአርሰናል መልዕክተኞች ከአለቃቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ የሚፈፅሙበት መንገድም ያስገርማል።
በዘመናዊ እግር ኳስ በሀያላኑ መካከል ያለው ልዩነት የመርፌ ቀዳዳ ያህል እየሆነ ነው። ይህንን ከጊዜ እና ቦታ ጋር አዋህዶ መጠቀም የብልህ አሰልጣኝ ውሳኔ ነው። አርቴታ እያደረገ ያለውም ያንን ነው።
የአርቴታ ቡድን የጨዋታ መንገድ ብዙ ትችቶች ቢነሱበትም፤ እንደ ቶኒ ፑሊስ አልያም ሞውሪኒሆ መከላከልና መግጨትን የሚወድ ነው ቢባልም እሱ ግን እንደ ሁኔታው እየሮጠ ነው።
አርሰናል ዛሬ ቀን 11:00 ከፉልሃም ጋር በሚያደርገው የጨዋታ መርሃግብርም የማርኮ ሲልቫ ትኩረት የአርሰናልን የቆመ ኳስ መከላከል እንደሆነ ተናግረዋል። በእርግጥ ሲልቫ ሌሎች የአርሰናል ጠንካራ ጎኖችንም አጥንተናል ብለዋል።
ከ14 ጨዋታዎች 22 ነጥቦችን የሰበሰበው ፉልሃም 9ኛ ደረጃ ላይ ነው። ካሸነፈ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ይላል። መድፈኞቹ በበኩላቸው ካሸነፉ ነጥባቸውን 31 በማድረስ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ ሊቨርፑልን ለመያዝ የሚያደርጉትን ጥረት ያጠናክራሉ።
ይህ ጨዋታ የሄል-ኢንድ ፍሬዎች የበለጠ የሚታዩበትም ነው። በአርሰናል ደጋፊዎች የሚወደደው ኤሚል ስሚዝ ሮው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደገበትን፤ የጎለመሰበትን የቀድሞ ክለቡን ይገጥማል። ስሚዝ ሮው በአርሰናል ዋናው ቡድን አጀማመሩ ድንቅ ነበር። ጉዳት ግን ፈተነውና ከብቃቱ መንሸራተት ጀመረ። ራሱን መልሶ ሊያገኝ ሲል ደግሞ የቡድኑ እድገት ለእሱ ቦታ ነፈገው። ባለፉት 2 አመታት ለአርሰናል የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያደረገው 525 ደቂቃዎች ብቻ ነው። እንደ ዘአትሌቲክ ዘገባ ተጫዋቹ በዚህ አመት ለፉልሃም በ14 ቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 1009 ደቂቃውችን ተሰልፏል።
አሌክስ ኢዎቢም የቀድሞ ክለቡን አርሰናልን ይገጥማል።
በቅርብ ጊዜያት ይህ ጨዋታ ለአርሰናል አስቸጋሪ ነው። ያውም ክራቨን ኮቴጅ ላይ ነው የሚደረገው። ባለፈው አመት
የማይክል አርቴታ ቡድን የትልልቅ ጨዋታዎች ቁልፍ የነበረው የቅመ ኳስ ፉልሃም ላይ አልሰራም ነበር። እንዴያውም በተቃራኒው ተቀጥቶበታል።
የአርቴታ ምስጢራዊ ማጥቂያ ኒኮላስ ጆቬር ዛሬስ ምን ይሰራ ይሆን?
ሀብታሙ ካሴ