የ60 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ውቢቷ አርባ ምንጭ

6 Days Ago 251
የ60 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ውቢቷ አርባ ምንጭ

አርባ ምንጭ ከተማ ከ60 ዓመታት በፊት በፊታውራሪ አዕምሮ ስላሴ አበበ እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡

አርባዎቹ ምንጮች ከሚፈልቁበት ስፍራ የተቆረቆረችው አርባ ምንጭ፤ የዓባያ ኃይቅ ከተንጣለለበት ቦታ፣ የነጭ ሳር ፓርክ ተስታኮ ካለው ስፍራ ላይ መስረታዋን አድርጋለች፡፡

የጥቅጥቅ ደኖችና ዕጽዋቶች መገኛ፣ የዓባያና ጫሞ ሐይቆችን የሚለየው የእግዜር ድልድይ መገኛ፣ የነጭ ሳር ፓርክ፣ በተራሮች ሰገነት የተከበበች ውብና ድንቅ ተፈጥሮን አቅፋ የያዘችውን አርባ ምንጭ ለመርገጥ ብዙዎች ይናፍቃሉ፡፡

አርባ ምንጭ ከተማ የቀድሞ ስያሜዋ "ጋንታ ጋሮ" ይባል እንደነበር የታሪክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከተማዋ አሁን የያዘችውን ስያሜዋን ያገኘችው በከተማዋ ከሚገኘው ጥቅጥቅ ደን በሚፈልቁ 40 ምንጮች መነሻነት ነው፡፡

ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺህ 285 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ፤ ከአዲስ አበባ በ 505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ 

በታላቁ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ “ሴቻ” እና “ሲቀላ” የተባሉት መንደሮቿ በከተማዋ በስፋት የሚታወቁት ሰፈሮች ናቸው።

ማራኪ ተፈጥሯዊ መልክአ ምድርን የታደለችው አርባ ምንጭ፤ የጋሞ አባቶች መገለጫ የሆነው የእርቅ ስርዓት "ዱቡሻ" መፍለቂያና የእንግዳ አክባሪ ህዝብም መገኛ ናት።

ከተማዋ ከሐይቅ ዳር፣ ውኃ ካለበት ወንዝ አካባቢ መመስረቷ ለኢኮ ቱሪዚም የምታበረክተው አስተዋጾ ከፍተኛ እንዲሆን ማስቻሉ ይነገራል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት የተከበበችው አርባ ምንጭ በርካታ ውብ የሆነ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች ውብ የተፈጥሮ ደንና እጽዋት ያላት ከተማ መሆኗም ለየት ያደርጋታል፡፡

ለአትክልትና ፍራፍሬ ተክል የተስማማ የአየር ንብረት ያላት አርባ ምንጭ፤ የማንጎ፤ የሙዝ፤ የአቮካዶ፤ የአፕልና የሽንኩርት ምርቶች መገኛ ናት፡፡

አርባ ምንጭ የአዞ ቆዳ አቅርቦት፤ የዓሳ ምርት ምንጭ፤ የበርካታ ቀንድ ከብት ስጋና የወተት ምርት ፀጋ ያላት ከተማም ናት፡፡

የአርባምንጭ ከተማ በተፈጥሮ መስህብ የተንበሸበሸች በመሆኑዋ በርካታ ተሪስቶች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ሲሆን ባለፉት አመታት ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችንና እንግዶችን ተቀብላ ደረጃቸውን በጠበቁ ማራኪ በሆኑ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶችና ሎጆች  አስተናግዳ ሸኝታለች።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የምትገኝው አርባ ምንጭ ከተማ የዘንድሮውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

19ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ነገ ለማክበር የተዘጋጀችው እንግዳ ተቀባይዋ የአርባ ምንጭ ከተማ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርጋለች።

በመሃመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top