"የሰላምን መንገድ የመረጥነው የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ነው"፦ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች

7 Days Ago 293
"የሰላምን መንገድ የመረጥነው የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ነው"፦ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች
የሰላምን መንገድ የመረጥነው የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ይህም አማራጭ የሌለው በመሆኑን ነው ሲሉ በቅርቡ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ገለጹ።
 
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች የሰላም ስምምነቱን አስመልክተው መግለጫ ሰጥዋል፡፡
 
መግለጫውን የሰጡት የሠራዊቱ ማዕከላዊ ዞን አዛዥ ጃል ሰኚ ነጋሳ፤ ስምምነቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ያሉ አሉባልታዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ተናግረዋል።
 
የሰላም አማራጭን የወሰዱት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ሰላምን በመምረጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
የሕዝብን ሕመም የማይታመሙ አካላት የሚያሰራጩት አሉባልታ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚያውቁ እና የሚረዱ ሳይሆኑ ሩቅ ተቀምጠው ጦርነት የሚቀሰቅሱ ናቸው ብለዋል፡፡
 
"አሉባልተኞቹ እንደሚሉት ስምምነቱን የፈረምነው መንግሥት ቀጥሮን ሌላውን ለማወናበድ አይደለም" ያሉት ጃል ሰኚ፤ ወደ ሰላም ስምምነቱ የመጡት የሕዝብን ጥያቄ በመቀበል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ለዚህ ደግሞ ማሳያው አሁን ወደ ካምፕ እየገባ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆኑን በመጥቀስ፤ አሉባልታውን ከሚያሰራጩት አካላትም እንዴት ወደ ሰላም መመለስ እንደሚችሉ ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ችግር ይህን አማራጭ እንድንመርጥ አድርጎናል ያሉ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል በሚደረገው ጦርነት እየተጎዳ ያለው የገጠሩ ሕዝብ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
 
በክልሉ ያለው ሁኔታ በጦር ሜዳ መፍትሔ እንደማያገኝ መረዳታቸውን እና ይህንን አማራጭ መውሰዳቸውንም አክለው ተናግረዋል፡፡
በሕዝቡ ላይ እየተሠራ ያለውን ግፍ ከሕዝቡ መረዳት ይችላል ያሉት ጃል ሰኚ፤ ሕዝቡ በማያገባው ጉዳይ መስዋዕትነት እየከፈለ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
 
ስምምነቱ ለሕዝቡ እፎይታን ያመጣል ብለን እናምናለን ሲሉም ጃል ሰኚ አክለዋል።
 
ስምምነቱን የተቀበሉት ታጣቂዎች ወደ ካምፕ እየገቡ እንደሆነ እና የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ እንሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡
 
የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በጋራ መልሶ መገንባት እና ቅራኔ የተፈጠሩባቸውን አካባቢዎችም ማስታረቅ የስምምነቱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
 
ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸው፤ ስምመነቱን የሚያስፈጽም ሦስት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በሰሞኑ ቆይታቸውም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ ልማቶችን መጎብኘታቸውን ያነሱት ጃል ሰኚ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች መልካም መሆናቸውን እና ከዚህ በተሻለ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
 
ሕዝብ ከጦርነት ይልቅ ከሰላም አትራፊ መሆኑን በመጥቀስ፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሀሳብ መፍታት የሰለጠነ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top