የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እድገት የሚያመጣ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ በመጀመሪያና በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የማማሻሻያ ሂደቱም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ፣ ዕዳን በማቃለል፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል የላቀ ጠቀሜታ አንዳለው አንስተዋል።
የፖሊሲ ትግበራው የዋጋ ንረትና የምንዛሬ ገበያ መዋዠቅን እንዲሁም የአጭር ጊዜ ጫናን በመቋቋም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ዋነኛ ዓላማው መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የፐብሊክ ፋይናንስ ስርአቷ የተሻለ ግልጽና ውጤታማ መሆኑን ገልጸው በዚህ ሪፎርም ጫና የሚደርስባቸውን ወገኖች የደሞዝ ጭማሪን ጨምሮ ድጎማ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀሳቦች ተቀርጸው ባለፉት ስድስት አመታት በተለያየ ደረጃ ሲተገበር መቆየቱን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም መዋቅራዊ በሆኑ የአሰራር ግድፈቶች ታንቆ የነበረውን የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት የኢኮኖሚው መሪ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
