የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን በማፍራት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

11 Mons Ago 187
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን በማፍራት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ብቁ የሕግ ባለሙያዎችን በማፍራት የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።  

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት 60ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሕግ ትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ጊዜ÷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በአገሪቱ ላሉ የሕግ ትምህርት ቤቶች መሰረት ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ ለፍርድ ቤቶች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራትና ለተለያዩ አካላት ተከታታይነት ያለው ሥልጠና በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ ትምህርት ቤቱ በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ብቃት ያላቸው ዳኞችን፣ ጠበቃዎችንና ዓቃቤ ሕጎችን በማፍራት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በቀጣይም ትምህርት ቤቱ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ክፍተቶችን በማረምና የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ብቁ ባለሙያዎች የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተቀዳጀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የሕግ ትምህርት ቤቱ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ካለው ቁርጠኝነት አንፃር የዩኒቨርስቲው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማግኘት እድገቱን ለማፋጠን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በመርኃ ግብሩ የቀድሞ ተማሪዎች መገኘት የትምህርት ቤቱን የስድስት አስርተ ዓመታት ጉዞ በግልፅ ለመገምገምና የተመራቂዎችን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ይሆናል ነው ያሉት።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top