ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሥራ መፍጠር እንደሚያስችል ተገለጸ

2 Mons Ago
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሥራ መፍጠር እንደሚያስችል ተገለጸ

ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚችል ሥራ ፈጣሪ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስችላል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ሁለተኛውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የመጀመሪያው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥልቀት ከተገመገመ በኋላ ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩን አስታውቀዋል። 

በሁለተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተወዳዳሪ የሥራ ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ምርትና ማርታማነትን ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናሉ ብለዋል። 

የኢኮኖሚ ማሻሻያው የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በማነቃቃትና የዕድገት ምንጮቻችንን በማስፋት ንቁና ተወዳዳሪ፣ የሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዝ ለመፍጠር ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል። 

በመጀመሪያው ዙር የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሴክተሮች የማምረት አቅም ላይ በሰፊው ትኩረት በመስጠት ተሠርቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአሁኑ ያገለገሉ ሥራ ፈጣሪዎቻችንን አቅም በማየት የማሳደግ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል። 

ዶክተር እዮብ እንዳመለከቱት፤ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከባቢ በማሻሻል በፈጠራ ላይ ኢንቨስት የማድረግ፣ በተለያዩ ዘርፎች አቅምን የመፍጠር፣ በምርምርና በልማት ላይ ኢንቨስት የማድረግ አቅሞች እንዲጠናከሩ ይደረጋል። 

መንግሥት በሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን ችግሮች ሊፈታ በሚችል መልኩ የግሉ ሴክተር ማድረግ ያልቻለውን ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል። 

የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማ ለማድረግ የሲቪል ሰርቪሱን አቅም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚችል የሥራ ፈጠራና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ጥረት ይደረጋል ብለዋል። 

በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግዙፍ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊና የሀገር ውስጥ ፈተናዎችን በመቋቋም በመጀመሪያው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል። 

ዶክተር እዮብ እንዳስታወቁት፤ የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አራት ቁልፍ ምሰሶዎች አሉት። 

በኢኮኖሚ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የግሉ ዘርፍ ንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የአየር ንብረትን በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ብቃት ያለው የሲቪል ሰርቪስ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። 

በንግዱ ዘርፍ የተሻለ ኢንቨስትመንት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዳለ ገልጸዋል። 

በሀገሪቱ የንግዱን ዘርፍ ለማሻሻል የፈቃድ አሰጣጥና የግብር አሠራሮችን ዲጂታል ማድረግ፣ የመንግሥት አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። 

በኢንቨስትመንት ዘርፉ ለባለሀብቶች የንብረት ጥበቃ፣ የሕግ ከለላና መተማመንን የማጎልበት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። 

የግል ዘርፍ፣ የሥራ ፈጠራ፣ የክህሎት ትኩረት ወሳኝ የኢኮኖሚ ድርሻዎች በመሆናቸው፤ በኢኮኖሚ ማሻሻያ ማጠቃለያው ንቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ ለመፍጠር እንደሚሠራ አስታውቀዋል። 

የሁለተኛው ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዕድን፣ በሎጂስቲክስ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። 

የግሉ ዘርፍና የሥራ ፈጠራው ሲታሰብ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሳሰረ ቁርኝት እንዳለው የተናገሩት ዶክተር እዮብ፤ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥቅም ላይ የዋለው ከ30 አስከ 40 በመቶ በመሆኑ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁለተኛው ማሻሻያ ለህዝብ ትልቅ ተስፋዎችን የያዘ በመሆኑ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል። 

የሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የ10 ዓመት የወደፊት ዕቅዶች ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በመጀመሪያው ዙር ማሻሻያና ያልተሟሉ ሥራዎችን ለማሳካትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሰፊ ሥራ ይከናወናል ሲሉ ተናግረዋል። 

ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የማክሮ ኮሚቴ፣ በገንዘብ እና በፕላንና ልማት ሚኒስትሮች የሚመራ የበይነ-ሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲሁም የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን የያዘ መሆኑንም ዶክተር እዮብ አመላክተዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top