የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት አከባበር ያለፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
በመስከረም ወር ሕዝብ በስፋት ወደ ጎዳና በመውጣት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ተጠቃሽ ናቸው።
የእነዚህ በዓላት አከባበር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ግብረ ኃይሉ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ፣ በተለይም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓልን በተመለከተም ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሸገር ከተማ ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፣ በእነዚህ የአደባባይ በዓላት አከባበር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የወንጀል እና የፀጥታ ስጋቶችን ለማስወገድ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተለያዩ አጋዥ ኃይሎችን ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እስከ ብሎክ በማደራጀት እና በማስተሳሰር ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በውይይቱ ላይ እንዳነሱት፣ በዓላቱን የማይመለከቱ እና የሌሎችን መብት እና ነፃነት የሚጋፉ ሐሳቦችን በጽሑፍም ሆነ በሌሎች ዓርማ እና ምልክቶች ማንፀባረቅ ክልክል በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ለፀጥታው ሥራ ሲባል በዓሉ በከተማ ደረጃ በሚከበርበት ስፍራ ፍተሻ ስለሚኖር የበዓሉ ታዳሚዎች ለፀጥታ አካላቱ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ኮሚሽነር ጌቱ አስረድተዋል።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የቅድመ መከላከል ሥራውን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን በመረዳት ኅብረተሰቡ እስካሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለቱ በሚከበሩበት ወቅት ምንም አይነት ርችት መተኮስ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ግብረ ኃይሉ አሳስቦ ይህንን በመተላለፍ ርችት ሲተኩስ የተገኘ ግለሰብ ሆነ ተቋም ላይ በህግ አግባብ እርምጃ የሚውስድ መሆኑን አስታውቋል።
ኅብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አስተላልፏል።