የአሜሪካው ኢስተርን ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

11 Mons Ago 199
የአሜሪካው ኢስተርን ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

በሀገረ አሜሪካ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ የካበተ ልምድ ያለው ኢስተርን ኮርፖሬሽን ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሰሩ ሰራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤቶችን ለመገንባትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የትራንስፎርሜሽን እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም ከተማ ከኩባኒያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቪድ ሃምና ልዑካቸው  ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የትራንስፎርሜሽን እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅ/ቤት ኃላፊው አቶ ፍፁም ከተማ ኢስተርን ኮርፖሬሽን በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት ለማድረግና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ያሳየውን ከፍተኛ ፍላጎት አድንቀዋል። 

ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመርና አጠቃላይ የሰራተኛውን ምቾት ለመጠበቅ የሚያግዙ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ፍፁም ኩባንያው ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የኢስተርን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቪድ ሃም በበኩላቸው ኩባንያው በአሜሪካን ሃገር በተለያዩ ግንባታዎች ላይ ያካበተውን ልምድ በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ማቀዱን ገልጸው፤ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክም ኢንቨስት በማድረግ በዘርፉ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ማቀዱን አሳውቀዋል።

ኢስተርን ኩባንያ በአሜሪካን ሃገር በቤቶች ግንባታ እንዲሁም በፕሮጀክት ማስተዳደር ዘርፍ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ሲሆን፤ ከ2000 በላይ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለደንበኞቹ ያስረከበ ግዙፍ ኩባንያ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top