የአይሪሽ ድንች ልማት እና ምርምር ማህበር ምስረታ መርሐ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል

1 Yr Ago 80
የአይሪሽ ድንች ልማት እና ምርምር ማህበር ምስረታ መርሐ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል

ማህበሩ በድንች ልማት ስራ ላይ የተሰማሩ 9 ድርጅቶችን ያቀፈ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም በድንች ልማት ዘርፍ የሚሰሩ አካላትን በማቀናጀት ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

ድንችን በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ3 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የሚመገቡት ሲሆን፤ ከስንዴ እና ሩዝ በመቀጠል በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል የምግብ ዓይነት ነው።

ከዓለም የድንች አምራቾች 42ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከዘርፉ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የአይሪሽ ድንች ልማት እና ምርምር ማህበር መመስረቱ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም በመርሐ-ግብሩ ተጠቅሷል።

የአይሪሽ ድንች ልማት እና ምርምር ማህበር በኢትዮጵያ የሚገኙ በድንች ልማት ላይ የተሰማሩ አምራቾች፣ ተመራማሪዎች፣ ማቀነባበሪያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሰሩ ለማድረግ ይሰራልም ነው የተባለው።

በሀገሪቱ ያለው ኋላቀር የድንች አመራረት በሄክታር ከ130 ኩንታል በላይ ምርት ማምረት የማያስችል ሲሆን፤ አሁን ላይ በሚደረጉ ምርምሮች በሄክታር እስከ 300 ኩንታል ማምረት እንደሚቻል ተረጋግጧል።

እነዚህን የምርምር ስራዎች ተደራሽ ለማድረግ ከአይሪሽ ድንች ልማት እና ምርምር ማህበር ጋር በመተባበር መስራት እንደሚያስፈልግም በመርሐ-ግብሩ ተጠቅሟል።

በስራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች የጥናት ፅሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሰለሞን ከበደ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top