ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት መመስረት ትሻለች - አንድሩ ሚሼል

10 Mons Ago
ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት መመስረት ትሻለች - አንድሩ ሚሼል

የዩናይትድ ኪንግደም የልማት እና የአፍሪካ ሚኒስትር አንድሩ ሚሼል መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳለው ገለፁ።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቬስትመንት፣ ደህንነት፣ ኢሚግሬሽን እና ሌሎች ዘርፎች የነበረው ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል ሚኒስትሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በኒውዮርክ ባደረጉት ውይይት።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በኤፕረል 2024 በዩናይትድ ኪንግደም በሚካሄደው የአፍሪካ የኢንቬስትመንት ጉባኤ እንድትሳተፍ መጋበዟንም አብስረዋል።

ሀገሪቱ በጉባኤው እንድትሳተፍ የተጋበዘችው በአፍሪካ ባላት ልዩ ቦታ እና ሚና መሆኑንም አንስተዋል።

ግብዣውን የተቀበሉት አቶ ደመቀ፤ ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት እና ሰብዓዊ አጋር ናት ብለዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያም ለአንድሩ ሚሼል ገለፃ አድርገውላቸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top