በጋምቤላ ክልል አሁን ያለውን ሰላም ለማፅናት ከማህበረሰቡ ተሳትፎ በተጨማሪ ጠንካራ የፀጥታ አካላት አደረጃጀት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ህዝባዊ የሰላም ኮንፍረንስ በክልል ደረጃ በጋምቤላ ለሁለተኛ ቀን በመካሄድ ላይ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ክልሉን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ስኬታማ ተግባር መከናወኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ሰላምን ለማፅናት የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲያበረክት ርዕስ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው፥ በክልሉ የተገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው በማስቻል የህዝቡ ደህንነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።