በ"ፋኖ" ስም እየተንቀሳቀሱ የሃገር ሰላም ለማወክ በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል- የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት

1 Yr Ago 473
በ"ፋኖ" ስም እየተንቀሳቀሱ የሃገር ሰላም ለማወክ በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል- የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት

አሁናዊ የመከላከያ ሰራዊቱን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የሰራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፣ መግለጫው በተለያዩ አካላት በሰራዊቱ ላይ እየተናፈሱ ያሉ ብዥታዎችን ለማጥራት የተሰጠ ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ ካለፉት ዓመታት በነበረበት ቁመና ላይ እንዳለ የሚያስቡ አካላት ካሉ የቆሙት እነርሱ እንጂ ሰራዊቱ ተራማጅ ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፣ ሰራዊቱ ዘርፈ ብዙ ግዳጁን እየተወጣ ነው ብለዋል።

"ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ" የሚል አካል ላይ ሰራዊቱ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ሰራዊቱን መቋቋም ያልቻሉ አካላት በሰራዊቱ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት።

በተለይ አሁን ላይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሸኔ የመደምሰስ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

በአማራ ክልል በመሬት ላይ ካለው ግጭት የገዘፈ የሚዲያ ትግል ተከፍቷል ተብሏል በመግለጫው።

ከሰሞኑ በጎንደር የሰሜን ምዕራብ እዝን ዓመታዊ አፈጻጸም ላይ ለመገምገም ወደ ስፍራው እያቀኑ በነበሩ የሰራዊቱ አባላት ላይ ከጩሂት 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርሱ ተኩስ በሰራዊቱ ላይ መከፈቱን ጠቅሰዋል።

የሰራዊቱ አባላትም በመመለስ ላይ ሳለም በቆላድባ አካባቢ በተመሳሳይ ተኩስ ተከፍቷል ነው ያሉት።

ለዚህም ሰራዊቱ ችግሩን በብልሃት ለመፍታት መስራቱንም አስታውሰዋል።

ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከወጣቶች እና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሂዶ እንደነበር እና በይቅርታ መዘጋቱን አንስተዋል።

በምስክር ስናፍቅ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top