“አምና የትምህርት ማህበረሰቡን ያስደነገጠው ውጤት ዘንድሮ ይሻሻላል ብለን እንጠብቃለን”፡- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

1 Yr Ago 639
“አምና የትምህርት ማህበረሰቡን ያስደነገጠው ውጤት ዘንድሮ ይሻሻላል ብለን እንጠብቃለን”፡- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

በ2014 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተመዘገበው አስደንጋጭ ውጤት ትምህርት በመውሰድ በተማሪዎች አመለካከት ላይ በተፈጠረው ለውጥ እና በትምህርት ቤቶች ሲደረግ በነበረው ዝግጅት ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። 

ሚኒስትሩ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በነበሯቸው ውይይቶች በ2014 የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት አብዛኛውን የትምህርት ማህበረሰብ ቁጭት ውስጥ የከተተ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀዋል። 

ሚኒስትሩ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለጹት፤ ውጤቱ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ከማስደንገጥ ባለፈ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ችግር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው።  

አምና ከተመዘገበው ውጤት በኋላ ሁለት መሰረታዊ ለውጦች መኖራቸውን ከነበረው አጠቃላይ ውይይት መረዳት መቻሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያውና ዋነኛው ተማሪዎች በኩረጃና በስርቆት ውጤት ሊመጣ እንደማይችል በመረዳት በራሳቸው አቅም ለፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል። 

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አምና ከተመዘገበው አስደንጋጭ ውጤት ብዙ ትምህርቶችን በመውሰድ ለተማሪዎች የሚሰጡትን ትምህርት በሚገባ በመፈተሽ የመማር ማስተማር ሂደቱን እና ተማሪዎችን ለፈተና የሚያዘጋጁበትን መንገድ እንዲያሻሽሉ ማስቻሉን ገልፀዋል። 

በትምህርት ቤቶች ሲደረግ የነበረው መሰል ዝግጅት እና በተማሪዎች አመለካከት ላይ የተፈጠረው ለውጥ በዚህ ዓመት የሚመዘገበውን ውጤት የተሻለ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል። 

ዘንድሮ እየተሰጠ ያለውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አስመልክቶ በሰነዘሩት ሃሳብ፥ የዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ከአምና ተሞክሮዎች በመነሳት በሰላም እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ይበልጥ በማሻሻል በቀጣይ ዓመታት ለተማሪዎች የሚሰጠውን ፈተና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

“ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ቃል በትምህርት ሚኒስቴር የተጀመረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የትምህርት ተቋማትን በማሻሻል በእውቀታቸውና በችሎታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር የሚያግዛቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ንቅናቄው ማህበረሰቡ ለትምህርት የሚሰጠውን ቦታ በመለወጥ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ትምህርት ቤቶቹን በእኔነት ስሜት እንዲመለከት እና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በሰለሞን ከበደ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top