በ2015 በጀት ዓመት 6 ሺህ 768 የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ

4 Mons Ago
በ2015 በጀት ዓመት 6 ሺህ 768 የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ

በተወሰደው ጥቃቶችን የማክሸፍ እርምጃም 23 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም አስተዳደሩ ጨምሮ ገልጿል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ የ2015 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ላይ 6 ሺህ 959 የሳይበር ጥቃቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ 768 የጥቃት ሙከራዎች ሲከሽፉ የተቀሩት 191 ጥቃቶች መሳካታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ ምላሽ የሚፈልጉትን በመለየት 96 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ተሰጥቶባቸው መጠናቀቁንና 3 ነጥብ 98 የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የሳይበር ጥቃቶች በመከላከል 23 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ነው አቶ ሰለሞን ያስረዱት።

የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ መሰረተ-ልማቶችን በማቋረጥ እና ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነት መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያ መንገድን በመጠቀም ገንዘብ በማጭበርበር እና ለመውሰድ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር ነው ያሉት።

የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ በባንኮችና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያደረጉ ሲሆን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ሚዲያ ተቋማት፤ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የሕክምና እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥቃቱ ዒላማዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በ2015 በጀት አመት በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረ-ገጽ ጥቃት፣ የመሰረተ ልማት ቅኝት፣ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ እና ሰርጎ መግባት ሙከራ በዋናነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ አገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 4 ሺህ 336 የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎች ውስጥ 583 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

አስተዳደሩ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚከናወነው ስራ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የሳይበር ምሀዳሩን ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top