የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ ለማድረግ የ36 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት ተፈረመ

4 Mons Ago
የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ ለማድረግ የ36 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት ተፈረመ

የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ ለማድረግ የ36 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት ተፈረመ

******************************

የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ ለማድረግ የ36 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት በመንግሥት እና በአጋር ድርጅቶች መካከል ተፈርሟል።

ለሦስት ዓመት የሚቆየውን ስምምነት በመንግሥት በኩል የፈረሙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው።

በአጋር ድርጅቶች በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ በፌት ፋውንዴሽን፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና የፓካርድ ፋውንዴሽን ሲሆኑ፤ የኔዘርላንድ መንግሥትም በቀጣይ በጀት ለመስጠት የስምምነቱ አካል ሆኖ ፈርሟል።

የሲቪክ ማኅበራትን በመወከል ደግሞ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ማኅበራት ጥምረት ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፥ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት እስከ ጤና ኤክስቴንሽን በሚደርስ መዋቅር እየተሠራ ቢገኝም፤ አሁንም አገልግሎቱን እየፈለጉ ተደራሽ ያልሆኑ 22 በመቶ ያህል ሴቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በነጻ የሚሰጥ እና ወጪው በአብዛኛው በለጋሽ አካላት የሚሸፈን በመሆኑ፣ የለጋሽ አካላት ድጋፍ በተለያየ ምክንያት እየቀነሰ በመምጣቱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት በመኖሩ ለግብዓት የሚያስፈልግ የበጀት እጥረት ማጋጠሙን አመልክተዋል።

ችግሩን በመቅረፍ አቅርቦቱ እንዳይቆራረጥ ለማድረግ በመደበኛነት ከሚመደበው በጀት በተጨማሪ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት መንግሥት 11.27 ሚሊዮን ዶላር፣ አጋር አካላት ደግሞ 24.8 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ የ36 ሚሊዮን ዶላር የተጨማሪ በጀት ስምምነት እና ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መደረጉን ጠቁመዋል።

ለቤተሰብ አገልግሎት መርሐ-ግብር ድጋፍ ለሚያደርጉ አጋር አካላት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በትንሽ ኢንቨስትመንት ብዙ እናቶችን መታደግ እንደሚቻል ጠቁመው፤ በሶማሌ ክልል በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝት በተደረገ የጋራ ርብርብ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ የነበሩ በርካታ እናቶችን መታደግ መቻሉን ማየታቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ አጋር አካላት በትብብር መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top