ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቤቱ አከማችቶ የተገኘው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

5 Mons Ago
ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቤቱ አከማችቶ የተገኘው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቤቱ አከማችቶ የተገኘው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

ፖሊስ በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ 64 የተለያዩ ዓይነት ሽጉጦች እና 587 የሽጉጥና የክላሽንኮቭ ጥይቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ በመጣስ  በቤቱ ውስጥ 197 ሺህ 400 ብር አስቀምጦ በመገኘቱ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር የዋለው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ አከማችቶ ማስቀመጡን ኅብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት በሰጠው ጥቆማ መሠረት፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በመኖሪያ ቤቱ በተደረገው ፍተሻ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።

በተጨማሪም ከተጠርጣሪው ጋር በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ግንኙነት ፈጥሮ ሲሰራ እንደነበር ኅብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሠረት፤ ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ባደረገው ብርቱ ክትትል በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪውን ከአንድ ማካሮቭ ሽጉጥ እና ከተመሳሳይ 20 ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራው እየተጣራ መሆኑን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተከማችቶ የተገኘው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በፀረ-ሰላም እጅ ቢገባ ኖሮ ጉዳቱ እጅግ የከፋ ይሆን እንደነበር የገለፀው ፖሊስ፤በቀጣይም ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በሀገርና በህዝብ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ተገንዝቦ ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ትብብር አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጥሪውን አቅርቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top