የሱዳን ተፈላሚ ኃይሎችን በአዲስ አበባ ለማነጋገር እየተሠራ ነው፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

1 Yr Ago 508
የሱዳን ተፈላሚ ኃይሎችን  በአዲስ አበባ ለማነጋገር እየተሠራ ነው፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የሱዳን ተፈላሚ ኃይሎችን  በአዲስ አበባ ለማነጋገር እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንቱ የተከናወኑ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የኢጋድ አባል ሀገራት ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በአዲስ አበባ እንዲያነጋግሩ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ባለፈው ሳምንት መሰየሙን አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።

በተለይም በሱዳን የሰብዓዊ ዕርዳታን ለማሳለጥ በሚቻልበት ሂደት ላይ ምክክር እንደሚደረግ እና ኢትዮጵያም የተለመደ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ከሰሞኑ በጅቡቲ የተካሄደው የኢጋድ መደበኛ የመሪዎች  ስብሰባ በብዙ መገለጫዎች ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።

ስብሰባው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የተሳተፉበት እንደነበር ያነሱት ቃል አቀባዩ፣ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በመሪዎች ደረጃ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት እንደነበር አንሥተዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኢጋድ አባል ሀገራት የባንዲራ ፕሮጀክት (Flagship Project) በመሆን በሁሉም አባል ሀገራት እንዲተገበር ከስምምነት መደረሱ ለኢትዮጵያ እና ለኢጋድ ትልቅ ስኬት ስለመሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ በድጋሜ የተመረጡበት እና የኤርትራ ከ16 ዓመታት በኋላ ወደ ኢጋድ መመለሷ ትልቅ ስኬት መሆኑን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በሳምንቱ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሳዑዲ ዓረቢያ በተካሄደው በዓለም አቀፉ የፀረ አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ስብሰባ ላይ መሳተፋቸው ተነሥቷል።

ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ከሳዑዲ ዓረቢያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ስኬታማ ውይይት አድርገዋል ተብሏል።

በተስፋዬ ጫኔ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top