መንግስት ለተለያዩ የሀይማኖት ተከታዮች የእምነት እና የመቃብር ቦታን የማመቻቸት ግዴታ አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

1 Yr Ago 525
መንግስት ለተለያዩ የሀይማኖት ተከታዮች የእምነት እና የመቃብር ቦታን የማመቻቸት ግዴታ አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው አቶ ሽመልስ ፣ሰሞኑን በተከሰተው አለመረጋጋት ለጠፋው የሰው ህይወትና በወደመው ንብረት ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
 
የተከሰተውን አለመረጋጋት ለማርገብ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኦሮሚያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላደረገው ጉልህ ድርሻ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደቀደመው ሁሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ ወሰን የሌለውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
ርእሰ መስተዳድሩ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት የከተሞች መስፋፋትን አሁን ካለበት 22 በመቶ ወደ 48 በመቶ በማሳደግ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመሬት አጠቃቀም እና መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የተዘጋጀው የመሬት አስተዳደር ህግ በጨፌ ኦሮሚያ ፀድቆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሸገር ከተማ ውስጥ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ለእስልምና፣ ለዋቄፈታ እና ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በቂ የግንባታ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አራት ዋናዋና ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንዲያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል፡፡
ከፕላን ውጭ የተሰሩ 656 የእምነት ቤቶች ወደ ወደ ፕላን እንዲገቡ ለማድረግ ጉባኤው ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን እንዲሰራ ነው ያሳሰቡት።
መንግስት በከተማ መሬት ስታንዳርድ እና በመሬት ህግ መሰረት ለሀይማኖት ተቋማት ግንባታ የሚውል ቦታ የሚሰጥ መሆኑን እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰፊ የአምልኮ ፣ የቱሪስት መስህብ እና የኮሌጅ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ መገንባት ለሚፈልጉ የሃይማኖት ተቋማት በልዩ ሁኔታ ቦታ ማዘጋጀቱ ተመልክቷል።
በተጨማሪም፥ የክልሉ መንግስት በህገ ወጥ ግንባታ ላይ የወሰደውን እርምጃ ያለምንም መደራደር እንደሚቀጥል እና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኦሮሚያ ፍትህና ጸጥታ ክላስተር ጋር ያለው መተባበር ሊጠናከር እንደሚገባም ርእሰ መስተዳደሩ መጠየቃቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top