አፍሪካ የውስጧን ችግሮች ካልፈታች እውነተኛ ነጻነት መጎናጸፍ እንደማትችል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

11 Mons Ago
አፍሪካ የውስጧን ችግሮች ካልፈታች እውነተኛ ነጻነት መጎናጸፍ እንደማትችል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
60ኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት - የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች በቂ ውክልናን ማግኘት እንደሚገባትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዛሬ 60 ዓመት 32 ነጻ የወጡ የአፍሪካ ሀገር መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሰርቱ ከቅኝ ግዛት በመላቀቅ ነጻነቷን የጠበቀች አፍሪካን አልመው ነበረ ብለዋል።
በዚያን ጊዜ የአፍሪካ ህዝብ ቁጥር 250 ሚሊዮን እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ ዛሬ 1.4 ቢሊዮን የሆነው የአፍሪካ ህዝብ እውነተኛ ነጻነትን ተጎናጽፎ የነዚያን ሩቅ አሳቢ አባቶች ህልም አላሳካም ብለዋል።
በ2050 ዓ.ም በዓለም ቀዳሚ የህዝብ ቁጥር የሚኖራት አፍሪካ፣ ተገቢውን ውክልና በዓለም መድረክ አላገኘችም ሲሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ገልጸዋል።
“ለመሆኑ በምግብ ራሳችንን ሳንችል፣ የውስጥ ችግሮቻችንን ሳንፈታ፣ አስተዳደሮቻችንን ሳናዘምን እንዴት ነጻ ነን ማለት እንችላለን? የቀድሞ አባቶቻችንን ህልምስ አሳክተናል ብለን እንዴት መናገር እንችላለን?” በማለት ጠይቀዋል።
አፍሪካ ወደፊት ለመራመድ ከፈለገች የወጣቶቿን አቅም መጠቀም አለባት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በውስጧ የያዘቻቸውን ሀብቶቿን ወደ ዕድል መለወጥ አለባት ብለዋል።
“ራሳችንን መመገብ ካልቻልን መቼም ነፃነታችን ሙሉ ስለማይሆን በምግብ ራሳችንን መቻል አለብን፤ ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል መንገዱን ጀምራለች። በግብርናው ዘርፍ እያመጣችው ያለው ለውጥ ለሌሎች አፍሪካውያን ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። በቀድሞ አባቶቻችን መንፈስ ተመርተን እውነተኛ ነጻነታችንን መጎናጸፍ አለብን” ብለዋል።
እስከዛሬ የሚነገርልን ታሪክ በራሳችን ሳይሆን በሌሎች የተቀረጸልንን ማንነት ነው፤ ይህ ማንነት ያለንን አቅም አሳንሶ እዚህ አድርሶናል፤ ከዚህም ለመውጣት እውነተኛ ህብረትና ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ መሥራት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፣ በቡድን 20 እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቂ ውክልና ማግኘት አለብን ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top