የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ተስማሙ

11 Mons Ago
የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ተስማሙ

በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ይሁን እንጂ ከተጀመረ አራተኛ ሳምነቱ ላይ የደረሰው የሱዳን ጦርነትን ለማስቆም በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪዎች መካከል ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ድርድር እስካሁን የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም።

ሁለቱ የሀገሪቱ ተፋላሚ ኃይሎች እስካሁን ተኩስ አቁም ላይ መድረስ አልቻሉም።

ከሱዳን ባሻገር ቀይ ባሕርን ተሻግራ በምትገኘው በሳዑዲዋ የወደብ ከተማ ጅዳ ውስጥ በተቀናቃኞቹ አንጃዎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ንግግር ያዘጋጁት ሳዑዲ ዓረቢያ እና አሜሪካ ናቸው።

አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት፣ ድርድሩ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ እና ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ ለመድረስ ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን “አሁንም ተራርቀው ነው ያሉት” ሲሉ ገልጸውታል።

ነገር ግን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላማዊ ዜጎች እና ለሰብአዊ ዕርዳታ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ስምምነት ፈርመዋል።

ተኩስ የማቆሙ ነገር ግን አሁንም እልባት ያላገኘ ሲሆን፣ ንግግሩ እየተደረገ በተለያዩ የሱዳን ክፍሎች ውስጥ ውጊያዎች አየተካሄዱ ነው።

ሁለቱ ኃይሎች አሁን በደረሱት ስምምነት መሠረት፣ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት በችግር ላይ ላሉ ሰዎች እንዲደርስ እና ውጊያን በመሸሽ ከአካባቢያቸው ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲንቀሳቀሱ ፈቅደዋል።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ የጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ የጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተወካዮች አሁንም ድርድራቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል።

ሁለቱ ወገኖች በዋናነት ለ10 ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም እንዲተገብሩ እና ተፈጻሚነቱን የመቆጣጠሪያ ዘዴ ላይ እንዲስማሙ አደራዳሪዎቹ ግፊት እያደረጉ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top