ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከዓለም አቀፍ የተራድዖ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

11 Mons Ago
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከዓለም አቀፍ የተራድዖ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተራድኦ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ፣ የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ውጤታማ እንዲሆን በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከጦርነት ምንም አይነት ትርፍ ስለማይገኝ በቁርጠኝነት የሰላም ስምምነቱ እንዲፈጸም እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም አይነት ልዩነት ቢኖር እንኳ በሰላማዊ አማራጭ ብቻ ልዩነቶችን ለመፍታት ቁርጠኛ ነን ሲሉም አክለዋል።

የተራድኦ ድርጅቶች በጦርነቱ ወቅት ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ወገኖች ስላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።

ከጦርነቱ ማግስት በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ነገር ግን የሚያስፈልገው ሀብት ክፍተኛ በመሆኑ አሁንም ሰፊ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ፣ የክልሉ መንግስት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች እንድናግዝ ምቹ ሁኔታወችን ስለፈጠረልን እናመሰግናለን ብለዋል።

ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የምግብ፣ የጤና እና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

አሁንም በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በመኖራቸው ወደ ቀያቸው መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በይኸነው ዋጋቸው


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top