አቶ ደመቀ መኮንን ከቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

11 Mons Ago
አቶ ደመቀ መኮንን ከቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
በአፍሪካ አራት አገራት ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ትናንት ወደ ቡሩንዲ፣ ቡጅምቡራ አቅንተው ከፕሬዚዳንት ኤቨርስቴ ንዳይሽሚዬ ጋር በሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የማፅናት እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኝነት ወስዶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የናይል ተፋሰስ አባል አገራት መደበኛው የምክክር ሂደት እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ከሱዳን ህዝብ ጎን እንደምትቆም ገልጸዋል።
የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ኤቨርስቴ ንዳይሽሚዬ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ዳግም አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለአፍሪካ ሰላም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ቡሩንዲ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚፈጠሩ ልዩነቶች ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ በውይይት መፍታት እንዳለባቸው እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።
በናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ ልዩነቶችን ሁሉም የተፋሰሱ አባል አገራት በውይይት መፍታት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሌሎች አባል አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ወንዙን ለልማት የመጠቀም እና የበርካታ ዜጎቿን ሕይወት ወደተሻለ ደረጃ የመለወጥ መብት አላት ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቡሩንዲ ጉብኝታቸው አስቀድሞ በታንዛንያ እና ኮሞሮስ ባደረጓቸው ጉብኝቶች ከአገራቱ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ በትብብር መሥራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top