“ከሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ ይጀመራል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

11 Mons Ago
“ከሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ ይጀመራል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ከሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ በታንዛኒያ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የወለጋ ሕዝብ እፎይ እንዲል ሁሉም ወገን የበኩሉን እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ 'ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና’ በሚል መሪ ሐሳብ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንን ቀንን እንድናይ ያደረገንን ፈጣሪ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያመሰግን ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ ብለዋል።
በሌላ በኩል በቀጣዩ ሣምንት በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የተመራ ልዑክ ወደ መቀሌ እንደሚያቀና ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለጹት።
ልዑኩ የሁሉንም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ያካተተ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እርዳታ ወደ ሱዳን ለመላክ ዝግጅት ስለማደረጉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይፋ አድርገዋል።
በዚህ የዕርዳታ ማዕቀፍ 50 ሺህ ኩንታል ስንዴ ወደ ሱዳን እንደሚላክ ነው ያስታወቁት።
የሱዳን ኃይሎች ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠብ አቁሞ ሰላም ለመፍጠር በቂ ያልሆነ ምክንያት እና ትክክለኛ ያልሆነ ጊዜ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሰላም ምክንያት አይፈልግም፤ ሰላም የተለየ ጊዜም አይፈልግም ነው ያሉት።
ዛሬ እየሆነ ያለው የሰላም መቋጫ እና የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ማብሰሪያ ዕለት ነው ብለዋል።
ሰላም ብርሃን ነው፤ የነገር ሁሉ መጀመሪያም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ ለዚህ ሰላም እንድንበቃ ላደረጋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top