በአማራ ክልል በ 5.3 ቢሊዮን ብር ለቀጣይ 7 አመታት የሚተገበር እና ከ7.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በባህር ዳር ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው ፕሮግራሙ የምግብ ዋስትናን በዓይነትና በመጠንም በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሰብል፣ በእንስሳትና፣ በአነስተኛ መስኖ ልማት በ45 ወረዳወች ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
በዚህ በሶስተኛው ምእራፍ የግብርና እድገት ፕሮግራም 11 አዲስ ወረዳዎች ተጨምረው በ9 ዞኖች እና በ48 ወረዳወች 7.8 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ 5.3 ቢሊዮን ብር ለቀጣይ 7 አመታት እንደሚተገበርም ነው የተገለጸው።