ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ

1 Yr Ago 553
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ፤ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ የሀገሪቷ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት ሥርዓት በመዘርጋት እና የተመዝጋቢዎችን መረጃ በመያዝ የዲጂታል መታወቂያ አጠቃቀም ስርዓትን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር ስርዓት እንዲዘረጋና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
አዋጁ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ እፀገነት፤ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የተጭበረበረ መታወቂያ ሰጥተው ከተገኙ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እና አስተማማኝነቱም በመርህ ላይ መመስረቱን አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top