ፈያ ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት ተቋም (ኤፍ አይ ዲ ኦ) በድርቅ እና በግጭት ምክንያት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ተቋሙ ለአንድ ዓመት በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ በድርቅ፣ በምግብ እጥረት፣ በግል እና አካባቢ ንፅህና ችግሮች እና በግጭቶች ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና እና የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ሲያቀርብ መቆየቱ ተጠቅሷል።
በዚህም ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።
የተቋሙ ለአንድ አመት ሲተገብረው የቆየው ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ እና የአዲስ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ ፈያ ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት ተቋም እና መሰል ሀገር በቀል ተቋማት ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ የኅብረተሰቡን የጤና ችግር ለመቅረፍ የሚያደረገውን ጥረት ለመደገፍ የጤና ሚኒስቴር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በሦስቱ ክልሎች በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአመጋገብ፣ ንፅህና አጠባበቅ እና የድንገተኛ አደጋ ግብረ መልስ ድጋፍ የሚያደርግበትን አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
በዚህ በሁለተኛው አዲስ ፕሮጀክትም ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ማቀዱን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።