ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያደርጉ የሚደረጉ ክልከላዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል፦ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

8 Mons Ago
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያደርጉ የሚደረጉ ክልከላዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል፦ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያደርጉ መከልከል፣ ወከባ እና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አሳሰበ።
ቦርዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የጉዳዩን አሳሳቢነት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የእናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በስላሴ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ ሊያደርገው የነበረው ስብሰባ ለጊዜው ስሙ ባልተረጋገጠ የሕግ አስፈጻሚ ኃላፊ ትዕዛዝ እንዳይካሄድ መደረጉን አንሥተዋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፖርቲ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም በጋምቤላ ሆቴል ሊያካሄድ የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ባልታወቀ የሕግ አስፈጻሚ አካል የሆቴሉ ባለቤቶች ላይ በደረሰ ማስፈራሪያ ሊካሄድ አለመቻሉንም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፖርቲ አስተባባሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ተካፍለው በማግስቱ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች እንደያዙ በፌዴራል ፖሊስ ታስረው ወደ ደቡብ ክልል ፖሊስ ተላልፈው እንደተሰጡ በመግለጫው ተነሥቷል።
በዚህም መሠረት ፓርቲዎች ጉባኤዎቻቸውን እንዳያደርጉ እና የጀመሩትን ጉባኤም ዳር እንዳይደርስ የሚደረግባቸው ወከባ እንግልት እና እስር በቦርዱ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው አቶ ውብሸት በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ስለዚህም ይህንን ጥፋት ያጠፉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ይህንን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እመቃ እንዲያስቆሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አሳስቧል።
በዮሐንስ ፍስሐ

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top