ባለፉት 6 ወራት ከሙስና ጋር በተያያዘ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ደላሎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

1 Yr Ago
ባለፉት 6 ወራት ከሙስና ጋር በተያያዘ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ደላሎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
በአዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ከሙስና ጋር በተያያዘ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ደላሎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን፤ ከንቲባ አዳነች የአስፈፃሚ ተቋማትን የ6 ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
በፀረ ሙስና ትግሉ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ደላሎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
እነዚህም 40 ከየካ፣ 42 ከነፋስ ስልክ ላፍቶ፣ 48 ከለሚኩራ፣ 33 ከአቃቂ ቃሊቲ እና 26 ከልደታ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ከማዕከል መሆናቸው ተጠቁሟል።
ስህተቶችን ለማረም የአመራር ማጠናከር ለአብነትም በየካ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች መከናወኑንም አመልክተዋል።
በ6 ወራቱ ለ200 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ከዕቅዱ በ100 ሺህ የላቀ ለማሳካት መቻሉም ተገልጿል።
በትራንስፖርት ዘርፍም የተበላሹ አውቶቡሶችን በማስጠገን እና ዘመናዊ አውቶቡሶችን በመግዛት አገልግሎቱን ለማሻሻል መቻሉን ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው አንስተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል፣ የሕግ የበላይነትን ማጠናከር፣ አማራጭ የመኖሪያ ቤቶችን ማቅረብ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እና ሌብነትን መታገል ከአስተዳደሩ ቀጣይ ቁልፍ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
በጥላሁን ካሳ

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top