ወደ መቐለ እና ሽረ በሚደረጉት በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው

1 Yr Ago
ወደ መቐለ እና ሽረ በሚደረጉት በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው
ወደ መቐለ እና ሽረ ከተሞች በሚደረጉት በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ።
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ እና ሽረ በሚያደርጋቸው በረራዎች በአዲስ አበባ እና በመቐለ ተመድበው የሚሠሩ አንዳንድ ባለሙያዎች እና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ጉዳይ እናስፈጽማለን ከሚሉ ግለሰቦች ጋር ተመሳጥረው ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ስለተደረሰባቸው ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ እና ኅብረተሰቡን ለእንግልት ሲዳርጉ የተደረሰባቸው በሙሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በጋራ እየተሠራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በቀን ወደ መቐለ የሚደረገው የበረራ ቁጥር ወደ አምስት ማደጉን እንዲሁም ወደ ሽረ የሚደረገው በረራም በሳምንት ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱን የጠቆመው መግለጫው፣ አስፈላጊው የሰው ኃይል በየበረራ መዳረሻው ተመድቦም ደኅንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ ተጓዦች በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑንም አመልክቷል።
ሆኖም በርካታ ሰዎች የአየር ትራንስፖርት የመጠቀም ፍላጎታቸው መጨመሩን እንደመልካም አጋጣሚ የወሰዱት በአዲስ አበባ እና በመቐለ የተመደቡ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዳንድ ሠራተኞች እና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ከጥቅም ተጋሪ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ እንደነበር ተደርሶበታል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው በድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩ አራት ግለሰቦች በመለየታቸው እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳያቸው መቐለ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝ መግለጫው አስታውቋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሠሩ የነበሩ አምስት ኤጀንቶች ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ ሲሆን፣ ሌሎች በጉዳዩ የተሳተፉ አካላትን በመለየት እርምጃዎች ለመውሰድ መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ኅብረተሰቡ በሕጋዊ አሠራር እና ይህንኑ ለማከናወን ከተደራጀ ቢሮ ብቻ ቀርቦ ትኬቱን በመቁረጥ በተቀመጠው የተቋሙ ታሪፍ ብቻ አገልግሎት ማግኘት የሚችል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፣ ባልተገባ መንገድ በሕገ-ወጦች ተታሎ እላፊ ገንዘብ እንዳይከፍል እና እንዳይጭበረበር መጠንቀቅ እንዳለበት አስገንዝቧል።
ከዚህ ውጭ ኅብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ ለማጭበርበር የሚሞክሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ በተቋሙ ነፃ የስልክ መስመር 910 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻልም ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ አመልክቷል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top