በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም የተፈታበት ሂደት ለመላ አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ ነው - ደቡብ አፍሪካ

9 Mons Ago
በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም የተፈታበት ሂደት ለመላ አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ ነው - ደቡብ አፍሪካ

በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም የተፈታበት ሂደት ለመላ አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ገለጹ።

በ36ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና በ42ተኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ አገራቸው ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ የሰላም ስምምነት መድረክ በማዘጋጀቷ መደሰቷን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ችግሩ በሰላም እንዲፈታ በአፍሪካ ህብረት በኩል ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያሳየውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡

በ42ተኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ መክፈቻ ላይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሰላም ስምምነቱን ሂደት በተመለከተ ያቀረቡት ሪፖርት አስደሳች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ሂደቱ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ የተከተለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

ይህ ተሞክሮ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካውያን ችግር ሲገጥማቸው ቁጭ ብለው የሚወያዩበት የካበተ ባህላዊ እሴት እንዳላቸው የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ይህን እሴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ለመፍታት የተከናወነው የሰላም ስምምነት ከአፍሪካ ባሻገር ለመላው ዓለም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን በዛሬው እለት የሚጠናቀቅ ይሆናል።

እንዲሁም የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top