አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ

1 Yr Ago
አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ

ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በፈረንሳይ በተካሄደው የ3 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ።

የወርቅ ደረጃ የተሰጠው እ.ኤ.አ. የ2023 የፈረንሳይ ሃውትስ ደፍራንስ አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር ተካሂዷል።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ድል ቀንቷቸዋል።

በውድድሩ በ3 ሺህ ሜትር ሩጫ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ3 ሺህ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል።

አትሌቱ 3 ሺህ ሜትሩን በ7 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ከ81 ማይክሮ ሰከንድ በመሮጥ ለ25 ዓመታት ተይዞ የነበረውን ሪከርድ በማሻሻል ጭምር ነው ያሸነፈው።

በዚህም አትሌት ለሜቻ የ3 ሺህ ሜትር ንጉስ የሚባለው ኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኮመን ለ25 ዓመታት ይዞት የቆየውን 7 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ከ90 ማይክሮ ሰከንድ በማሻሻል ነው አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበው።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፥ በሌሎች ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ድል የቀናቸው ሲሆን፤ በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

በዚህ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በአንደኝነት አጠናቃለች።

ጉዳፍን በመከተል አትሌት ሂሩት መሸሻ ሁለተኛ ስትሆን፤ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ እና አክሱማይት አምባዬ ሦስተኛ እና አራተኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቀዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top