ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማከናወን የነቃ ተሳትፎ ታደርጋለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

1 Yr Ago 319
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማከናወን የነቃ ተሳትፎ ታደርጋለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማከናወን የነቃ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ የሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በተለይ ከነገ ጀምሮ በሚካሄዱት 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 42ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ ያተኮረ ነበር።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፥ 35 ርዕሰ-ብሔሮች፣ አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ 11 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ 13 ቀዳማዊ እመቤቶች እና 10 የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊችን ጨምሮ የ51 አገራት የልዑካን ቡድኖች ጉባኤውን ይታደማሉ ብለዋል።

መድረኩ በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የሚካሄድ እና አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዎች የሚያከናውኑበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አገራትና ድርጅቶችም መድረኩን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት ገልፀዋል።

በመድረኩ ቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኮሞሮስ ከሴኔጋል ኃላፊነት ትረከባለች ብለዋል።

ጉባኤው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አተገባበርን በተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በስፋት እንደሚመክር ተናግረዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማከናወን መዘጋጀቷን ገልጸዋል።

በውጭ ግንኙነት ላይ ከአገራት መሪዎች ጋር ጠቃሚ ውይይቶች እንደምታደርግ እና የአረንጓዴ አሻራ ልምዷን እንደምታካፍልም ቃል-አቀባዩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማት የሰላም ችግር በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እንዲፈታ ለተደረገው ጥረትም አገሪቱ ምስጋና ታቀርባለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጉባኤው የፀጥታ ምክር ቤት ማሻሻያ እና የተለያዩ የሕግ ሰነዶች ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top