የሕወሓት ዕብሪት ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንዲታጠፉ እያስገደደ ነው!፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

31/08/2022 01:25
የሕወሓት ዕብሪት ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንዲታጠፉ እያስገደደ ነው!፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
መንግሥት ለሰላም አማራጭ ዕድል ለመስጠት ሲል የሕዝብ ማዕበል አስነሥቶ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አረጋውያንን ለመማገድ የመጣውን የሕወሓት ታጣቂ፣ በምሥራቅ አማራ በኩል በጀግንነት ሲከላከል ቆይቷል። ሕወሓት በምሥራቅ አማራ በኩል በቆቦና አካባቢው የከፈተው ወረራ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና በደጀኑ ሕዝብ ጠንካራ የመከላከል ብቃት የተነሣ ባሰበው ልክ አልሄደለትም። በዚህም ምክንያት ለሰላም የተሰጠውን ሁለንተናዊ አማራጭ አሽቀንጥሮ ጥሎ ወረራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ ይገኛል። ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ሕወሓት በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል። ይሄንን የሕወሓት ወረራ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱበትን ጥቃቶች በጽናት እየተከላከለ፣አሁንም ለሰላም አማራጮች የዘረጋቸውን እጆች ዛሬም ድረስ አላጠፈም። ለሰላም የተዘረጋው እጅ በሕወሓት ዕብሪታዊ ወረራ ምክንያት እንዳይታጠፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቻለውን እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም ያሳስባል። ወገናችን የሆነው የትግራይ ሕዝብም ይሄንን የዕብሪት ወረራ በማውገዝ ሕወሓት ከሚያስከትልበት መከራ ራሱን ነጻ እንዲያወጣ ጥሪ እናቀርባለን።
 
 
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የተመረጡ አጫጭር የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የቲክቶክ አካውንታችንን ይከተሉ
ግብረመልስ
Top