ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችን በውዴታ መቀበሏ ለአንድነቷ አጋዥ ሆኗታል" - ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

04/08/2022 09:54
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችን በውዴታ መቀበሏ ለአንድነቷ አጋዥ ሆኗታል" - ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖችን በውዴታ የተቀበለች ሀገር መሆኗ ለአንድነቷ ምስጢር ሆኗታል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናን ወቅቱን ያገናዘበ አስተምህሮ ማድረስ ይጠበቃቅባቸል ብለዋል።  በኢትዮጵያ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት ብዙ ክፍለ ዘመን ያስቆጠሩ እና አኩሪ ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቷ፤ የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ከማንም በላይ እጅግ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ታዳጊ ሀገር እድገትና ልማት ትሻለች ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ይህን እድገት ለማምጣት የሁሉም ርብርብና አንድነት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ነው የገለፁት። በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንደሚለሱ ለማደረግ ከፍተኛ ስራ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ሰቆቃዎች እየተበራከቱ በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች ሰብዓዊነትን እንዲላበሱ ለማድረግ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ፕሬዝዳንቷ የተናገሩት።
 
በመሐመድ አልቃድር
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የተመረጡ አጫጭር የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የቲክቶክ አካውንታችንን ይከተሉ
ግብረመልስ
Top