በኮንሶ ዞን ከና ወረዳ እንደ ዘመን መለወጫ የሚከበረውን የ‘ቱታ’ በዓል በቅርስነት ለማስመዝገብ ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ

1 Yr Ago
በኮንሶ ዞን ከና ወረዳ እንደ ዘመን መለወጫ የሚከበረውን የ‘ቱታ’ በዓል በቅርስነት ለማስመዝገብ ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ
በኮንሶ ዞን ከና ወረዳ ሕዝብ ዘንድ እንደ ዘመን መለወጫ የሚከበረው የ‘ቱታ’ ክብረ በዓል በዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ። የ"ቱታ" ክብረ በዓል በኮንሶ ዞን ከና ወረዳ ኢትዮጵያዊ ስሜትን በተላበሰ መልኩ በፋሻ ከተማ ተከብሯል። በኮንሶ ዞን ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የቱታ ክብረ በዓል በዞኑ ከና ወረዳ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው እና ብዙ ዘመናትን የተሻገረ ክብረ በዓል ነው። ክብረ በዓሉ በየዓመት ሐምሌ ወር የሚከበር ሲሆን ሕዝቡ ፈጣሪ በዓመቱ ስለሰጣቸው ምርት፣ ጤና እና ሰላም እንዲሁም ቸርነት ምስጋና የሚያቀርቡበት፤ በቀጣይ አዲሱ ዓመት ጥሩ ምርት እንዲገኝ፣ በሽታ እና ክፋት ከሕዝቡ እንዲርቅ እና ሰላም እንዲሰፍን አምላካቸውን የሚማፀኑበት ልዩ ክብረ በዓል እንደሆነ በኮንሶ ዞን የባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግሥቱ ህርቦ ተናግረዋል። ክብረ በዓሉ የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር እና መተሳሰብ የሚጎልብትበት፤ የተኳረፉ አርቅ የሚፈጽሙበት፣ ከአንድ ማዕድ የሚቆርሱበት በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ልዩ ትርጉም አለው ያሉት የከና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጎዳና ኮሻና፣ ይህ እንቁ የሆነው ሀብት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል። የከና ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካልማሌ ካፖሌ በበኩላቸው፣ ክብረ በዓሉ በውስጡ የማይዳሰሱ በርካታ ሥርዓቶችን የያዘ እና በአከባቢው ብቻ ሳይሆን በሀገር አንድነት፣ ፍቅር እና ይቅርታ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችል በዓል ነው ብለዋል። የቱታ ክብረ በዓል እንደ ኦሮሞ ኢሬቻ፣ እንደ ሲዳማው ፍቼ ጫምባላላ እና እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክብረ በዓላት በኮንሶ የከና ወረዳ ሕዝብ ዘንድ በልዩ ትኩረት የሚከበር በዓል ነውም ብለዋል። ክብረ በዓሉ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ እና ከሕዝቡ ጋር አብሮ የነበረ ቢሆንም እንብዛም የማስተዋወቅ ሥራ ያልተሠራበት በመሆኑ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠራበት መናገራቸውን ደሬቴድ ዘግቧል። በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህል አባቶች የአሁኑ ትውልድ ለቀጣይ ትውልድ ባህላዊ እሴቱን ሳይበርዝ እና ሳያዛንፍ የማስተላለፍ አደራ እንዳለበት ጠቁመዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top