በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ ቀጥሏል!” - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

1 Yr Ago
በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ ቀጥሏል!” - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ የሚገኘው የተቀናጀ እርምጃ በአኩሪ ድል ታጅቦ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል። ከቀናት በፊት "አቶ" በሚባለው ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ገብቶ በነበረው የአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ አብዛኛው የቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ ሸሽተው ተደብቀው የነበሩ 25 የሽብር ቡድኑ አባላት ላይም እርምጃ ተወስዷል። በደረሰበት የተቀናጀ የማጥቃት እርምጃ የተበተነው ጥቂት ሃይልም የያዘውን ከባድ መሳሪያ መጨረሱንና ባገኘበት ቦታ ለመደበቅ እየሞከረ ይገኛል። እስካሁንም የሽብር ቡድኑ ይዞት ከመጣው 4 የረጅም ርቀት መገናኛ ሬዲዮ ውስጥ ሶስቱ ተማርከዋል። ፌርፌር በተባለው አካባቢ በኩል ገብቶ ከነበረው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ውስጥም በ85ቱ ላይ እርምጃ ተወስዶ ሸሽተው ወደመጡበት ሲመለሱ በነበሩትም ላይ የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ፌደራል ሃይል የማያዳግም እርምጃ ወስዶባቸዋል። እስካሁንም ድንበር ጥሶ ከገባው ታጣቂ ኃይል ውስጥ ከ209 በላይ የሚሆኑት በክልሉና በፌደራል የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ እርምጃ መደምሰሳቸው ታውቋል። በክልሉ ህዝብና ሚሊሻ እርምጃ የተወሰደበት እና የተማረከውን የሽብር ቡድኑ አባላት ትክክለኛ ቁጥርም እየተጣራ ይገኛል። የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከረው የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በክልሉ ልዩ ኃይል አኩሪ ተጋድሎና በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ የሰው ሃይልና የንብረት ኪሳራ ደርሶበታል። ይህ የሽብር ቡድን በኤልከሬ ወረዳ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሌላኛው የሽብር ቡድን ከሸኔ ጋር ለመገናኘት አልሞ የነበረ ቢሆንም ይህ እቅዱ ሙሉ በሙሉ መክሸፉ ተረጋግጧል። በተቀናጀው የመልሶ ማጥቃት የተበታተነውና ተቆርጦ የቀረውን የሽብር ቡድኑ ኃይል ላይ የሚወሰደው የማጽዳት ተልእኮ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ይቀጥላል። የሽብር ቡድኑ ይዞት የመጣውን የሽብር ተልእኮ ሙሉ በሙሉ በማክሸፍ እና አሁንም ገብቶባቸው ከነበሩት አካባቢዎች በማጽዳቱ ሂደት ከጸጥታ ኃይሉ ባሻገር የአካባቢው ህዝብ አስተዋጽኦ እና መስዋእትነት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ይህ ቡድን ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ እስኪጠናቀቅም ህዝቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top