ዩክሬን የእህል ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ መላክ እንድትችል መግባባት ላይ ተደረሰ

22/07/2022 01:42
ዩክሬን የእህል ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ መላክ እንድትችል መግባባት ላይ ተደረሰ
ዩክሬን የእህል ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ መላክ እንድትችል ከሩሲያ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ቱርክ አስታወቀች። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በዩክሬን፣ ሩሲያ፣ ቱርክ እና የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መካከል ዛሬ ዓርብ በኢስታንቡል ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል።
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተጀመረበት ከባለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የእህል እጥረት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረኃብ ስጋት ዳርጓል። ጦርነቱ የእህል ዋጋ እንዲያሻቅብ ምክንያት በመሆኑም የዩክሬን ወደቦችን ክፍት ማድረግ እና ሀገሪቱ የእህል ምርቶቿን ወደ ውጭ እንድትልክ ማስቻል እጅግ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል። በአሁኑ ሰዓት 20 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የእህል ክምችት በኦዴሳ ወደብ ላይ የሚገኝ መሆኑ ተጠቅሷል። የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተመድ መሪነት የሚደረግ ሌላኛው ዙር ውይይት በቱርክ እንደሚካሄድ አረጋግጧል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስክይ በበኩላቸው፣ “ወደቦቻችንን ዳግም የመክፈቱን ዜና ሀገራችን በጉጉት የምትጠብቀው ነው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የዩክሬን የፓርላማ አባል ስምምነት ይደረጋል የሚለው ጉዳይ ላይ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል። “ስምምነቱ እስካሁን አልተደረሰም”፣ ያሉት የኦዴሳ የፓርላማ አባል ኦሌክሲ ሆንቻሬንኮ፣ “ሩሲያን በፍፁም የማናምናት በመሆኑ ይህ ስምምነት እስከሚፈረም መጠበቅ ግድ ይለናል” ሲሉ አክለዋል።
ዩክሬን የእህል ምርቷን ወደ ሌሎች ሀገራት እንድትልክ የሚያስችላት ስምምነት ከተደረሰ የተቀመጡ ዕቅዶች ምን እንደሆኑ ዲፕሎማቶች ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት፦ የዩክሬን መርከቦች እህል የጫኑ መርከቦችን ፈንጂ በተጠመደባቸው የወደብ አካባቢዎች እንዲወጡ እና እንዲገቡ መንገድ ይመራሉ። ይህ ሲሆን ሩሲያ መርከቦቹን ላለመምታት የተኩስ አቁም ለማድረግ ትስማማለች። ቱርክ ደግሞ በተመድ አጋዥነት መርከቦቹ የጦር መሣሪያዎችን ስላለማጓጓዛቸው ቁጥጥር ታደርጋለች፣ ይህም የሩሲያን ስጋት ለመቀነስ ያሰበ ነው ተብሏል። ስምምነቱ ሩሲያም እህል እና ማዳበሪያን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ሌሎች ሀገራት እንድትልክ የሚያመቻች እንደሆነም ተገልጿል።
ግብረመልስ
Top