ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቀረቡት ዕጩ ኮሚሽነሮች መካከል 42ቱን መለየቱን አስታወቀ

2 Yrs Ago
ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቀረቡት ዕጩ ኮሚሽነሮች መካከል 42ቱን መለየቱን አስታወቀ
 
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል 42ቱን መለየቱን የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
አፈ-ጉባኤው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ቁጥር 1265/14 መቋቋሙንና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዕጩ ኮሚሽነሮች እንዲጠቆሙ በሁሉም ሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን መተላለፉን አንስተዋል፡፡
የጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜው እንዲራዘም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት በአካልና በጽሁፍ በጠየቁት መሰረት የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ም/ቤቱ ለአንድ ሳምንታት ማራዘሙን እና ባለፉት ሳምንታትም ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የም/ቤቱ ጽ/ቤት የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ሲቀበል መቆቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች 632 የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ ማቅረባቸውንና አብዛኛዎቹ ስራውን ለመስራት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት ያላቸው መሆኑን መገንዘብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ ለአፈ-ጉባኤውና ለአፈ-ጉባኤው ጽ/ቤት በሰጠው ስልጣን እንዲሁም በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከቀረቡት 632 ዕጩዎች መካከል 42ቱ መለየታቸውን ክቡር አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡
በቀረቡት 42 ዕጩ ኮሚሽነሮች ላይ ከአማካሪዎች ጋር ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሳምንትም የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አመራር አካላት በሚገኙበት በዕጩዎች የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ላይ ምክክር ተደርጎ ግብአት የሚሰበሰብ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በም/ቤቱ ድረ-ገጽና በማህበራዊ ሚዲያ የእጩዎችን ማንነት በመግለጽ በቂ ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ሰብሳቢና ም/ሰብሳቢን ጨምሮ 11ዱ ዕጩ ኮሚሽነሮች ለም/ቤቱ ቀርቦ ከፀደቀና ዕጩዎች ከተሰየሙ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባም መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ከህዝብ የሚነሱ የተለያዩ ሀገራዊ ሀሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው ሀገሪቱ ትልቅ ታሪክ፣ ህዝብ፣ ስነ-ልቦና እና ሀብት ያላት በመሆኑ ሁሉም አካል የሰከነ ውይይት በማድረግ እና መግባባት ላይ በመድረስ የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው አፈ ጉባዔው አሳስበዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top