ኢትዮጵያውያኑ የሴቶችና የወንዶች የ5ሺህ ሜትር ውድድር ክብረ ወሰንን ሰበሩ

04/01/2022 01:21
ኢትዮጵያውያኑ የሴቶችና የወንዶች የ5ሺህ ሜትር ውድድር ክብረ ወሰንን ሰበሩ
|እጅጋየሁ ታዬ እና በሪሁ አረጋዊ

ኢትዮጵያውያኑ እጅጋየሁ ታዬ እና በሪሁ አረጋዊ የዓለም የአምስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ክብረ ወሰን መስበራቸውን የዓለም አትሌቲክስ የበላይ አካል አስታወቀ።

ትናንት አርብ በፈረንጆቹ አቆጣጠር የዓመቱ የመጨረሻ ዕለት በአውሮፓዊቷ ስፔን ባርሴሎና ከተማ በኩርሳ ዴልስ ናሶስ በተካሄደ ውድድር ነው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ክብረ ወሰን የሰበሩት።

በሴቶቹ እጅጋየሁ ታዬ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ እንዲሁም በወንዶቹ በሪሁ አረጋዊ በ12 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በማጣናቀቅ ነው ቀደም ሲል በርቀቱ የተያዙትን ክብረ ወሰኖች ያሻሻሉት።

በሴቶቹ የአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የዓለምን ክብረ ወሰን ያሻሻለችው እጅጋየሁ ታዬ ቀደም ሲል ከነበረው ሰዓት ላይ በ24 ሰከንዶች ቀድማ ገብታለች። በሪሁ አረጋዊም ክብረ ወሰኑን ያሻሻለው በሁለት ሰከንዶች መሆኑን የዓለም አትሌቲስ አስታውቋል።

የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ የ21 ዓመቷ እጅጋየሁ ታዬ የኢትዮጵያ የ3ሺህ ሜትር ርቀት ባለ ክብረ ወሰን መሆኗን አስታውሶ፤ ክብረ ወሰኑን አስክታሻሽል ድረስም በአምስት ሺህ ሜትር ውድድር የዓለም ሁለተኛዋ ፈጣን ሯጭ ሆና ቆይታለች ብሏል።

እጅጋየሁ የአምስት ኪሎ ሜትር ክብረ ወሰንን ያሻሻለችበት የባርሴሎናው ውድድር በሩጫ ዘመኗ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ የውድድር ተሳትፎዋ ነው።

የሃያ ዓመቱ በሪሁ አረጋዊ በኅዳር ወር ሊል ውስጥ በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ላይ በኬንያዊው ጆሽዋ ቼፕቴጌ ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን ለመስበር በአንድ ሰከንድ ተቃርቦ ነበር።

ነገር ግን የፈረንጆቹ 2021 ከመጠናቀቁ በመጨረሻዋ ዕለት በመጨረሻው ውድድር በሪሁ ከወር በፊት ተቃርቦ የነበረውን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ችሏል።

በተለመደው የዓለም አትሌቲክስ አሰራር መሠረት ይህ በሁለቱ ኢትዮጵየውያን አትሌቶች የተሻሻለው ክብረ ወሰን የሚጸድቀው አስፈላጊው የማጣራት ሂደት ከተካሄደ በኋላ ነው።

ግብረመልስ
Top