ይሄንን በማድረጉ በብዙ የተሞገሰውን ያህል ብዙዎች ደግሞ ትችት ሰንዝረውበታል፡፡ የተወለደው በጃማይካ ኪንግስትን ነው፡፡ የቀድሞው የሊቨርፑል እና የማንችስተር ሲቲ አጥቂ ራሂም ስተርሊንግ፡፡ አትሌት ከሆነች እናቱ የተወለደው ራሂም ስተርሊንግ አባቱን በሞት ያጣው ገና የሁለት አመት ልጅ እያለ ነው፡፡
ከኪንግስተን በ5 አመቱ ከእናቱ ጋር ወደ እንግሊዝ ያመራው ስተርሊንግ ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀው በለንደን አልፋና ኦሜጋ በተባለ አካዳሚ ነው፡፡ በኪው ፒአር አካዳሚ 8 አመታትን ያሳለፈው የመስመር አጥቂ በሊቨርፑል እና በማንችስተር ሲቲ ቤት ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡
ስተርሊንግ አባቱ የሞተው ሽጉጥ ተተኩሶበት ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ያለ አባት እንዲያድግ የተገደደው ራሂም ስተርሊንግ ይህንን ዕውነት የተረዳው ትልቅ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ በጃማይካ ተወልዶ በእንግሊዝ ያደገው ፈጣኑ አጥቂ በሁለት አመቱ በሞት ላጣው ወላጅ አባቱ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የቀኝ እግሩ ላይ የጠመንጃ ምስል ተነቅሷል፡፡
ተጫዋቹ ለመጀመርያ ጊዜ ከ2018ቱ የሩሲያ አለም ዋንጫ በፊት ልምምድ ላይ እያለ ንቅሳቱ ከታየ በኋላ በርካታ ትችቶች ሰንዝረውበታል፡፡ “ያለ አባት እንዳድግ የሆንኩት በመሳሪያ ምከንያት ነው” የሚለው ራሂም ስተርሊንግ እንዲህ አይነት መሳሪያ በፍጹም በእጁ ላለመንካት ለራሱ ቃል መግባቱን ተናግሯል፡፡ "በቀኝ እግሬ ላይ ምስሉን የተነቀስኩት አባቴን ያጣሁበትን መሳሪያ ሰውን ሳይሆን ሜዳ ላይ ኳስ ለመምታት እጠቀምበታለሁ" በማለት መሳሪያን መጠቀም ቀርቶ በእጁ ለመንካት እንኳን እንደማይፈቅድ በተደጋጋሚ ይናገራል።
የተነቀሰበት በቂ ምክንያት ያለው ራሂም ስተርሊንግ ተችዎቹ ማድረግ አልነበረብህም ቢሉትም እሱ ግን መሳሪያ በተነቀሰበት እግሩ በተጫወተባቸው ታላላቅ ክለቦች ተአምር ሰርቶበታል። መሳሪያን ለኳስ መጫዎቻ ብቻ እያለ በእግሩ ሰላም የሚሰብከው ስተርሊንግ ምንም እንኳ የመሳሪያ አድናቂ ነው ብለው ሰዎች ቢያወሩበትም እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው:: የልቡን የውስጡን ሃዘን ይዞ መሳሪያ አላስፈላጊ ነው ሲል የአባቱን ሞት እያስታወሰ የጠፋበትን መሳሪያ እግሩ ላይ ይዞ ይዞራል:: አንዳንዴ የሚወዱትን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉትንም ነገር ይዞ መኖር የሚገባው እንዲህ ባለው አጋጣሚ ነው:: እሱ የሚጠላውን ለሰዎች መማሪያነት ይህን አድርጏልና::