ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን - ዲጂታል ቱሪዝም

10 Days Ago 237
ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን - ዲጂታል ቱሪዝም
ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽ፣ የተፈጥሮ እና ታሪካዊ ሀብቶች ቢኖሯትም፤ ፀጋዎችን በማልማት እና ለዓለም በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ገቢ በተገቢው ልክ እያገኘች አለመሆኑ ይገለጻል፡፡
 
በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በርካታ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆችው ሀገር ኢትዮጵያ፣ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ግን ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡
 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝሙ ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የቱሪስት ማዳረሻዎችና መዝናኛ ሥፍራዎች በከፍተኛ ወጪ እየተገነቡ እንዲሁም እድሳት እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
 
በዚህም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቱሪስቶች ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡
 
ሀገሪቷ ያሏትን የቱሪዝም ፀጋዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተገቢውም መንገድ ለዓለም ባለመተዋወቁ እንዲሁም ተዋናዮች በቅንጅት መስራት የሚችሉበት አሰራር ባለመኖሩ ጎብኚዎች ስለኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች የተሟሉ መረጃዎች በቀላሉ እንዲየገኙ ማድረግ አልተቻለም ነበር፡፡
 
በሀገሪቱ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን፣ ምርቶችና አገልግሎቶችን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና የተሟላ መረጃ በቀላሉ ተዳራሽ ማድረግ አለመቻል ከሚስተዋሉ ክፍተቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
 
በተጨማሪም በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያን እንደ አየር መንገድ፣ አስጎብኝ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እንዲሁም የቱሪስት ትራንስፖርት አቅራቢዎች የሚተሳሰሩበት አንድ የዲጅታል ፕላትፎርም አለመኖርም እንደ ክፍተት ይጠቀሳል፡፡
 
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢንፈርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በጋራ ባለድርሻዎችን በማሳተፍ ዓለም አቀፍ ልምድ በመውሰድ 'ቪዚት ኢትዮጵያ' የተሰኘ የዲጅታል መተግበሪያ በትላንትናው እለት በይፋ ስራ አስጀምሯል፡፡
 
አዲሱ ድረ-ገፅ ቁልፍ የቱሪዝም ተዋንያን በአንድ ስፍራ በበይነመረብ ተገናኝተው አገልግሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ለመሸጥ እንዲሁም ከቱሪስቶች ጋር ለመገናኛት የሚያስችል ነው።
 
ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ሀብቶች አልምታ በማስተዋወቅ መጠቀም እንድትችል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒትሯ ሰላማዊት ካሳ ገልጸዋል፡፡
 
የቱሪዝም እንዱስሪውን ተወዳደሪ ለማድረግ ፈጠራ የተሞላባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም ግዴታ የሆነበት ዘመን ላይ ነን ያሉት ሚኒስትሯ፤የቱሪዝም ልማት ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ካልተቻለ እንደ ሀገር ሊገኝ የሚገባውን ገቢ ማግኘት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
 
'ቪዚት ኢትዮጵያ' ፕላት ፎርም ለዲጅታል መገበያያ የሚያገልግል (መስኮት) ሲሆን በዘርፉ ያሉ ተዋናዮችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top