አህጉር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንዳሉት ኮንፍረንሱ "የበለፀገና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ" በሚል መሪ ቃል ህዳር 16 እና 17 ይካሄዳል።
የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዚህ ኮንፍረንስ ላይ 22 የአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወቁት።
ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ በሚኒስትሮች የሚወከሉ ሲሆን አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቶችና በሰላም ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ተካፋይ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ከአራት መቶ በላይ ተሳታፊዎችም በሰላም ጉዳይ ላይ ይመክራሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሰፊ ልምድ እንዳላት ያነሱት ሚኒስትር ደኤታው፤ ሀገሪቱ ለቀጠናው፣ ለአህጉሪቱ ብሎም ለአለም ሰላም መጠበቅ ያበረከተችው አስተዋፅኦ የሚቀርብበት መድረክ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
ባለፉት አመታት ሀገሪቱ የገጠሟትን ፈተናዎች በምክክር ለመፍታት እየተሰራ ያለውን ስራ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጉባኤው ላይ እንደሚያካፍልም ገልፀዋል።
ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሀገራት ያለፉበትን መንገድ ተሞክሮ ያካፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልዕክት የሚያስተላልፉ ሲሆን ኢጋድን ጨምሮ ቀጠናዊ ተቋማት በሰላም ኮንፍረሱ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
በወንድወሰን አፈወርቅ