Search

ኢትዮጵያ የበኩሏን እየተወጣች ነው፤ ዓለምስ መቼ ወደ ተግባር ይገባል?

ሓሙስ ኅዳር 03, 2019 258

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ከወደፊት ስጋትነት አልፎ የዛሬው ትውልድ የህልውና ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት ሀገራት ከቃላት ባለፈ ተጨባጭ የተግባር እርምጃ እንዲወስዱ የኢትዮጵያ መልዕክት በዓለም አቀፍ መድረኮች በጎላ ሁኔታ እየተደመጠ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት "መጪው ጊዜ ከአቅም በላይ ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን ለማድረግ፣ የበካይ ጋዝ ልቀትን በፍጥነት መቀነስ ያስፈልገናል ኢትዮጵያ የበኩሏን እየተወጣች ነው" ብለዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታላቅ ማንቂያ ደወል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በተግባር ያረጋገጠችውን የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያመላክት ጥልቅ መልዕክት ያለው ነው።

የመጪውን ትውልድ ህልውና ከአስከፊ የአየር ንብረት ቀውስ ለመታደግ ዓለም የኢትዮጵያን ተሞክሮ እንደ አርአያ መውሰድ አለበት።

 የበካይ ጋዝ ልቀትን ዛሬ በፍጥነት አለመቀነስ ነገ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በምግብ እጥረት እና በኢኮኖሚ ውድመት የሚከፈለውን ዋጋ ከሰው ልጆች የመቋቋም አቅም በላይ ያደርገዋል።

የበለጸጉት ሀገራት ለኢንዱስትሪ ዕድገት ሲሉ የሚለቅቁትን በካይ ጋዝን ካልቀነሱ ቀውሱ ድንበር ሳይለይ መላውን ዓለም ወደማይወጣበት አዘቅት ይከትተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ይህንን አይቀሬ አደጋ ዛሬውኑ በተግባር እንድንቀለብሰው የሚያሳስብ ነው።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሙቀት መጨመር የምታበረክተው የበካይ ጋዝ ልቀት እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ችግሩን በመከላከል ረገድ ግን ከፊት ተሰልፋ እየመራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በውኃ፣ በንፋስ እና በፀሐይ ኃይል ላይ ያተኮሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ከ90 በመቶ በላይ የኃይል አቅርቦቷን ከብክለት ነጻ አድርጋለች።

የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል በአንድ ሀገር ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ሞዴል መከተል ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ልማትን እና የአካባቢ ጥበቃን አጣምሮ ማስኬድ እንደሚቻል በተግባር ያሳየች ሲሆን፣ ሀገራት የኢትዮጵያን የችግኝ ተከላ ባህል፣ የንጹህ ኃይል ሽግግር እና ሕዝባዊ ንቅናቄን ወደ ሀገራቸው ከወሰዱ፣ የበካይ ጋዝ ልቀትን በፍጥነት በመቀነስ መጪውን ጊዜ መታደግ ይቻላል።

ኢትዮጵያ በ32ኛው የዓለም አየር ንብረት ጉባኤን (COP32) ለማስተናገድ ስትዘጋጅ ለዓለም የምታቀርበው ዋናው አጀንዳ ይህንኑ በተግባር የታየ ልምዷን ነው። ሀገራት ምድራችንን ለማዳን ዛሬውኑ ከአዙሪቱ ወጥቶ ወደ ተግባር መግባት አለባቸው።

 በሃና ምንዳሁን

 

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: