Search

ከ48 ቢሊዮን እስከ አዲሱ የ8 ቢሊዮን ግብ፡ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ታሪካዊ ጉዞ

ረቡዕ ሐምሌ 22, 2018 149

ኢትዮጵያ 2011 . በይፋ የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ ከተካሄዱ ታላላቅ ሀገራዊ ንቅናቄዎች አንዱ ነው።

በተለይም በየዓመቱ የሚካሄዱት "የአንድ ጀምበር" የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች በግዙፍ የሕዝብ ተሳትፎ እና በአስደማሚ የአፈፃፀም አቅም የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት ያስጠሩ ታሪካዊ ኩነቶች ናቸው።

በሐምሌ 22 ቀን 2011 . የተካሄደው የመጀመሪያው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዘመቻ፣ የኢትዮጵያውያንን የሕብረት አቅም ለመላው ዓለም ያሳየ ነበር።

በዕለቱ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በሁሉም ህብረተሰብ ተሣትፎ በተደረገው ከፍተኛ ንቅናቄ እቅዱን በማስበለጥ 353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ተችሏል።

ይህም የኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ጉዞ በጠንካራ መሠረት ላይ የጣለ ትልቅ ስኬት ነበር። ከአራት ዓመታት አረንጓዴ ልማት በኋላ፣ በሐምሌ 10 ቀን 2015 . በድጋሚ የተካሄደው የአንድ ጀምበር ዘመቻ አዲስ የዓለም አቀፍ ድንቅ ታሪክ ጽፏል።

በዚሁ ቀን 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ታላቅ ግብ ተይዞ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣ ጀምበር ስትገባ ግን 566 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ሀገራዊ የታሪክ ምዕራፍ ተመዝግቧል።

በዚህ ዘመቻ 30 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያየ የሀገራችን ክፍሎች ወጥተው መሳተፋቸው የተገኘውን ድል የበለጠ አጉልቶታል።

በነሐሴ 17 ቀን 2016 . የተካሄደው ዘመቻ ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን የትግበራ አቅም ወደ አዲስ ደረጃ ያሸጋገረ ነበር።

በዕለቱ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ በዕለቱ በተመዘገበው ሰፊ ሕዝባዊ ማዕበል 615 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

ይህም ቁጥር ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር በርካታ ችግኞችን የመትከል እና የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብ ባህሏን ምን ያህል እንደገነባች ማረጋገጫ ሆኗል።

ሐምሌ 24 ቀን 2017 . ኢትዮጵያውያን የለመዱትን ገድል የፈጸሙበት ዕለት ነበር፡፡ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 717 ሚሊዮን ችግኞች የተተከሉበት ሌላኛው አስደናቂ ዕለት ሆኖ አልፏል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች።

በዚህ መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከል የሚለው ወቅታዊ ጥሪ እና ለዘንድሮው መርሐ ግብር 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው፣ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ ወደ ላቀ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ክስተት ነው።

ይህም ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠትና ለወደፊቱ ትውልድ ምቹ አካባቢን ለማስረከብ የያዘችውን ጽኑ ዓላማ ዳግም የሚያረጋግጥ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: