Search

በምክክር መድረኩ የተለያዩ አካላት ፍትሐዊ ውክልና አግኝተዋል - የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ቅዳሜ ሐምሌ 18, 2018 101

እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክሩ ሒደት ላይ የተሳታፊዎች አደረጃጀት ፍትሐዊነትን የተላበሰ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አረጋግጠዋል።

በቡድን ድልድሉ ወቅት የተፈጠሩ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ በማረም በእያንዳንዱ አጀንዳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተመጣጠነ ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኞች እና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማረፊያን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊው የተግባር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የተሳታፊዎች ስብጥር እና ፍትሐዊ ውክልና በተግባርም ትርጉም እንዲኖረው የውይይት ሒደቱ ተሳታፊዎችን 500 እስከ 10 አባላት ባሏቸው ንዑሳን ቡድኖች በመከፋፈል ሁሉም አካል ሐሳቡን በነጻነት እንዲገልጽ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ዋና ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

በምክክር ሒደቱ መነሻ ላይ የሐሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች መፈጠራቸው የሚጠበቅ እና የሒደቱ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ በመነሣት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሃይማኖት ተቋምም ሆነ ሌላ አካል በሌላው ላይ የሐሳብም ሆነ የቁጥር ብልጫ ወስዶ ጫና እንዳያሳድር ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ አካል ጉዳተኞች፣ የተገፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ከምንጊዜውም በላይ በእኩልነት እና በመከባበር አጀንዳዎቻቸውን እያብላሉ እንደሚገኙ እና አጠቃላይ ሒደቱም እጅግ አበረታች መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመግለጫቸው አክለው አስገንዝበዋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: