ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆኑትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርትአፕ ሠልጣኞች አስመርቃለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት የሠለጠኑትን የሀገራችንን የመጀመሪያዎቹን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስታርትአፕ ሠልጣኞች አስመርቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን የወደፊቱን ዕጣ ፈንታቸውን እና መዳረሻቸውን ሌሎች እንዲወስኑ ሳይጠብቁ በራሳቸው ጥበብና ዕውቀት እንደሚቀርጹ ገልጸዋል።
ይህ ታሪካዊ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዘርፉ የሰጡት ልዩ ትኩረት እና ክትትል፣ እንዲሁም ሀገራችን በልጆቿ ጥረት ያስመዘገበችው ትልቅ የስኬት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በስማርት ሲቲ፣ በፋይናንስ እና በሌሎችም ዘርፎች የተሠማሩት እነዚህ ወጣት ፈጣሪዎች በቆይታቸው የቴክኒክ እና የምርት ልማት ክሂሎት እንዲሁም ችግር ፈቺ የቢዝነስ አስተሳሰብ ሥልጠናዎችን ወስደዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወርክሾፕ፣ የክላውድ ዳታ ማዕከል እና ከፍተኛ የኮምፒዩቲሽናል ሪሶርስ ድጋፍ ማግኘታቸው ተገልጿል።
መንግሥት ለስታርትአፖች ድጋፍ ማድረግ የላቀ ቴክኖሎጂን ከማፍለቁም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ያመነ በመሆኑ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም የዚህ ትኩረት ተጨባጭ ማሳያ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: