Search

“ኢትዮጵያ ፈተና ቢበዛባትም ፈተናን በመሰባበር የማለፍ ተፈጥሮ ያላት ሀገር ናት” - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ቅዳሜ ሐምሌ 18, 2018 96

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሆለታ በሚገኘው የአካዳሚው ግቢ ያሠለጠናቸውን 71 ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን እያስመረቀ ይገኛል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ኢትዮጵያ ፈተና ቢበዛባትም ፈተናን በመሰባበር የማለፍ ተፈጥሮ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑ ያንገበገባቸው ባንዳዎች ኢትዮጵያን ለመፈተን ብዙ ሠርተዋል ያሉት ኢታማዦር ሹሙ፣ ነገር ግን ሀገርን እያዳነ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ብዙ የመመከት ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።

በዚህ ዘመን ፈተናን በመሰባበር ለማለፍ በሰው ሀብት እና በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት እና ሥልጠና ተቋማት ላይ ሠርተናል ሲሉም አክለዋል።

መከላከያ ሠራዊት የሰው ሀብት ልማት ላይ በመሥራቱ ሠራዊቱ እየዘመነ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚም በርካቶችን በማፍራት ሀገርን እያገለገለ ይገኛል።

ከራስ በላይ ለሀገር በሚል ራሳቸውን ለሀገራቸው አሳልፈው የሰጡ ዐርበኛ መኮንኖችን እያፈራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ለሲቪል ማኅበረሰብ በተሰጠው ዕድልም በርካታ ወጣቶች አካዳሚውን ተቀላቅለዋል ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

በሐሳብ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሠራዊትን ለማፍራት አሁንም ከአካዳሚው ማኅበረሰብ እንደሚጠበቅ በማሳሰብም አደራቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያዊነት ጽናት እና ሥነ ምግባርን በመላበስ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ሲሉም ለተመራቂ መኮንኖቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከልም ከደቡብ ሱዳን፣ ከታንዛኒያ፣ ከሶማሌላንድ እና ከሩዋንዳ የመጡ መኮንኖችም ይገኙበታል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ የመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሀብታሙ፣ የክብር ጄኔራል መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።

ከዚህ ቀደም የገነት ጦር አካዳሚ ይባል ነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ፣ ከተቋቋመ 91 ዓመት አስቆጥሯል። አካዳሚው እንደ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ያሉ በርካታ የሀገር ባለውለታዎች አፍርቷል።

በመቅደላዊት ደረጀ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: